ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የጥምቀት በዓልን ለማክበር ወደ ጎንደር የሚመጡ ታዳሚዎችን ለመቀበል ከተማዋ ዝግጁ መሆኗን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ገለፁ፡፡
በጎንደር በየዓመቱ በድምቀት ለሚከበረው የጥምቀት በዓል ወደ ከተማዋ የሚገቡ ታዳሚዎች በዓሉን በጥሩ ሁኔታ አሳልፈው እንዲመለሱ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በተለይ ለኢቲቪ ተናግረዋል፡፡
ከተማዋ ለመስህብነት የሚውሉ በርካታ ቅርሶች እና አቅሞች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፤ የበዓሉ ታዳሚዎች እነዚህን መስህቦች መጎብኘት የሚችሉበት አጋጣሚም እንደሆነ ነው የገለጹት።
በአካባቢው የሚስተዋሉትን ግጭቶች በመግታት ዘላቂ ሰላም ለማስፈንም እየተሰራ ስለመሆኑም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጠቅሰዋል፡፡
ለግጭት መንስኤ የሆኑ ነጥቦች መለየታቸውን እና ከማህበረሰቡ ጋር ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጠቁመዋል፡፡
ከልማት ጥያቄዎች ጋር ተያይዞ በአፋጣኝ ምላሽ ማግኘት ያለባቸው ችግሮች ላይ መስራት እንደሚገባ ገልጸው፤ ችግሮችን በመፍታት ከተማዋ ያላትን እምቅ አቅም መጠቀም ይገባል ብለዋል።
የጥምቀት በዓልን ለማክበር ጎንደር ዝግጁ ናት ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፤ በዓሉን የሚያከብሩ ወደ ከተማዋ እንዲመጡ ጥሪ አቅርባለሁ ብለዋል፡፡