የኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረበት 55ኛ ዓመት በዓልና የቻይና አዲስ ዓመት በወዳጅነት አደባባይ እየተከበረ ነው።
በዝግጅቱ ላይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይ ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በዚሁ ወቅት፤ የኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይፋ ከሆነበት ከአውሮፓውያኑ 1970 ወዲህ እያበበ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በመተማመን፣ በመከባበር እና በጋራ ራዕይ ላይ በመመስረቱ በማንኛውም ሁኔታ የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት ላይ መሸጋገሩንም ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቻይና ቤጂንግ በ2023 ያደረጉት ታሪካዊ ጉብኝት የሀገራቱን አጋርነት ይበልጥ ከፍ ያደረገ መሆኑንም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።
ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ በአውሮፓውያኑ 1971 በቤጂንግ ካደረጉት ጉብኝት አንስቶ ሁለቱ ሀገራት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በመሳሰሉ አለም አቀፍ መድረኮች ያላቸው ትብብር፣ እኩልነት፣ ከጣልቃ ገብነት የፀዳ እና የጋራ ተጠቃሚነት መርሆዎች ምሳሌ የሆነ ነውም ብለዋል።
ቻይና ግዙፏ የኢትዮጵያ የንግድ አጋርና ቀዳሚ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መገኛ ናት ያሉት አምባሳደሩ፤ የቻይና ባለሀብቶች በግብርና፣ በማዕድን፣ በማምረቻ ዘርፎች እንዲሁም ቱሪዝምን በመሳሰሉ ቁልፍ ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሀይ በኩላቸው፤ ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎችን ባለፉት አመታት ማከናወናቸውን ገልፀዋል።
በወንደሰን አፈወርቅ