መንግሥት ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ የገባው በጥናት ላይ የተመሰረተ በቂ ዝግጅት አድርጎ ነው - ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

1 Mon Ago 546
መንግሥት ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ የገባው በጥናት ላይ የተመሰረተ በቂ ዝግጅት አድርጎ  ነው  -  ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

መንግሥት ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በማለም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ የጀመረው በጥናት ላይ የተመሰረተ በቂ ዝግጅት አድርጎ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ገለጹ። 

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ መግባቷን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ በኢትዮጵያ የነበረው ተጨባጭ የኢኮኖሚ ሁኔታ አገሪቱ ልትደርስበት ያሰበችውን እድገት ለማሳካት የማያስችል በመሆኑ የለውጡ መንግሥት ይህን ለመቀየር የመጀመሪያውን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረጉን አስታውሰዋል።

በወቅቱ የአገር ውስጥ ገቢና ከውጭ የሚገባው ፋይናንስ አነስተኛ መሆን፣ ዝቅተኛ የፕሮጀክት የመፈጸም፣ የፖሊሲ ማነቆዎችን ጨምሮ መዋቅራዊ ችግሮች፣ የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው መሪ አለመሆን፣ ምርትና ምርታማነት ማነስና የሥራ እድል ፈጠራ መቀዛቀዝ የኢኮኖሚው ዋነኛ መገለጫዎች እንደነበሩ ገልጸዋል።

ይህንን ችግር ለማቅለል መንግሥት አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በመቅረጽ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቅሰው በተለይም በመጀመሪያ ምዕራፍ በሦስት ምሰሦዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።

በዋናነትም በማክሮ ፋይናንስ ዘርፍ የፊስካል ፖሊሲ (የመንግሥት ወጪና ገቢን) በተመለከተ የመንግሥት ገቢ አስተዳደር በማዘመን ለውጥ ማምጣት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ጎን ለጎንም የመንግሥት ወጪን በማስተዳደር በተለይም ኢንቨስትመንት እንዲሻሸልና ፕሮጀክቶች በታለመላቸው የጊዜ ገደብ፣ ጥራትና ገንዘብ እንዲጠናቀቁ በማድረግ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል። 

ከዚህ አንጻር፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የነበረባቸውን ሥር የሠደደ መዋቅራዊ ችግር በመፍታት ትርፋማ መሆን መቻላቸውን ገልጸው የንግድ ብድርን ሙሉ በሙሉ በማስቀረትና የእዳ ክምችትን በመቀነስ ረገድ ትልቅ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በመዋቅራዊ ዘርፍም በርካታ የሕግ ማዕቀፎችን በማሻሻል፣ የአገሪቱን የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢ ምቹ በማድረግ፣ እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና ተወዳደሪነትን በመፍጠር እመርታ መጥቷል ብለዋል።

አሁን ላይ በመጀመሪያው የአገር በቀል የኢኮኖሚ መሻሻያ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠልና ችግሮችን ለመፍታት መንግሥት ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ መግባቱን ጠቅስዋል።

ውሳኔው ወቅታዊና ኢትዮጵያ ለምታልመው ብልጽግና ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ ለመግባት ላለፉት አምስት ዓመታት ከአገር ውስጥና ከውጭ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ጥናት መደረጉን ጠቅሰው ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተጓዳኝ ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎችም በጥናት ተመላክቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ በአራት ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥንና አሁንም አገሪቱን እየፈተኑ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመፍታት በሂደት ተገማችና የተረጋጋ የማክሮ የኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲኖራት ያስችላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል። 

በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የዋጋ መዛባትን በማስተካከል፣ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በማጠናከር፣ የውጭ ሓዋላን በማሳደግ፣ ሕገ-ወጥና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን በመግታት ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል ብለዋል።

የአገሪቱን የማኅበራዊ ልማት ሥራዎችን በማሳለጥ በድኅነት ቅነሳ ላይ ተጨባጭ አዎንታዊ ለውጥ እንደሚያመጣም አስረድተዋል።

እንዲያም ሆኖ ሲንከባለሉ የመጡ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው እንቅፋት እንዳይሆኑ በተለይም የተቋማት ሪፎርም መጀመሩን ጠቅሰው ተቋማት በብቁ ባለሙያዎች እንዲደራጁ የማድረጉ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል።

የመንግሥት አገልግሎቶች በዲጂታል ሥርዓት እንዲደገፉ የተጀመረው ሥራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።   

የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳደር ዝቅተኛ የደሞዝ ተከፋይ ለሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ በማድረግ ተጓዳኝ አሉታዊ ጫናዎችን ለመቋቋም ጥረት እንደሚደረግ ዶክተር ፍጹም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ልማታዊ የሴፍቲኔት መርኃ ግብር እንደሚጠናከርና እንደ ነዳጅና ማዳበሪያ በመሰሉ ሸቀጦች ላይ መንግሥት አስፈላጊውን ድጎማ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።


Feedback
Top