ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዕድገት ሳይሆን ተዓምር ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

يوم 1 أيام
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዕድገት ሳይሆን ተዓምር ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዕድገት ተዓምራዊ ለውጥ ነው ሲሉ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተዓምራዊ ለውጡ ከለውጡ ጠንሳሾች ፍጥነት እና ጥራት በላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህንን ዕድገት በተገለጠ ዐይን ማየት እና መጠበቅ እንዲሁም መደገፍ ካልተቻለ አደገኛ መከራ ሊያመጣ እንደሚችልም ነው ያነሡት።

“ኢትዮጵያ ያንን ተዓምር ዘንድሮ ከደገመች መከራዋ ያበቃል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሊደጋገሙ ይገባል ያሏቸውን ስኬቶች ጠቅሰዋል።

ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 15 ዓመታት ኢትዮጵያ ከውጭ ንግድ ያገኘችው 7.5 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን በአንድ ዓመት ከ8 ቢሊዮን ዶላር እየተገኘ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከቡና በ15 ዓመታት 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር አግኝታ ዘንድሮ ግን በአንድ ዓመት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን ተናገረዋል።

ሀገሪቱ ዘንድሮ ከወርቅ የወጪ ንግድ ያስገባችው 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ለ15 ዓመታት ከወርቅ ኤክስፖርት አድርጋ ካገኘችው በ6 እጥፍ እንደሚበልጥም ነው የጠቆሙት።

“በተገለጠ ልቦና ማየት የሚፈልግ 15 ዓመታት ሙሉ እንደዚህ ዓይነት ተዓምር ሠርተንበት ቢሆን ኖሮ ዛሬ የት እንሆን ነበር? ብሎ ይጠይቃል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የተገኘውን ስኬት ለቀጣዮቹ አምስት እና 10 ዓመታት ከደገምነው ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብለዋል።

“ልክ እንደዘንድሮ አራት አምስት ዓመታትን ከደገመች የኢትዮጵያ መከራው አበቃ፤ ዘንድሮን መደጋገም ግን የጋራ ራዕይ፣ የጋራ ጥረት፣ የጋራ ሥራ መሆን አለበት” ሲሉም አሳስበዋል።

በፋሲካው ታደሰ

 


ردود الفعل
Top