የዘንድሮው የአካባቢ ጥበቃ "የፕላስቲክ ብከለትን ለመቀነስ ምላሽ ሚያስፈልጋቸው 10 አጣዳፊ ጥያቄዎች" በሚል መሪ ቃል እየታሰበ ይገኛል።
ዕለቱ በኮሪያ ጄጁ የደሴት ከተማ እየተካሄደ ሲሆን፣ የተመድ አካባቢ ጥበቃ ዋና መሥሪያቤት በሚገኝባት የኬንያዋ ናይሮቢ እና በድርጅቱ የኒው ዴህሊ ቢሮም ውይይቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ።
በኮሪያ እየተካሄደ ባለው ፎረም ወጣት የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች የፕላስቲክ ብክለትን በመቋቋም ረገድ ሊደረጉ በሚገባቸው ጥንቃቄዎች ላይ ያላቸውን ሃሳብ እያጋሩ ነው።
ዓለማችን ባለፈው ዓመት ብቻ 400 ሚሊዮን ቶን የፕላስቲክ ቆሻሻን አመንጭታለች። ይህ የፕላስቲክ ቆሻሻ ካባቢን በመበከል የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳርን አደጋ ውስጥ በማስገባት ለዓለም ስጋት እየፈጠረ ይገኛል።
የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም (UNEP) የሀብት እና ገበያ ኃላፊ የሆኑት ኤሊሳ ቶንዳ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የፕላስቲክ ብክለትን አስመልክተው፣ "የፕላስቲክ ብክለት በምድር ላይ ከተጋረጡ ከባድ የአካባቢ ሥነ-ምህዳር አደጋዎች አንዱ ነው፤ ነገር ግን ልንፈታው የምንችለው ችግር ነው" ብለዋል።
ኃላፊዋ እንደሚሉት በፕላስቲክ ብክለት የሚመጣውን አደጋ ማስቀረት የሰዎችን እና የፕላኔታችንን ደኅንነት ከማሻሻል ባለፈ በርካታ ኢኮኖሚያዊ እድሎች አሉት።
በአሁኑ ጊዜ የዓለም ሀገራት የፕላስቲክ ብክለትን ለማስቆም አስገዳጅ ዓለም አቀፍ የሕግ ስምምነትን እንዲኖር በመደራደር ላይ ናቸው። ከዚህ አንጻር፣ የዘንድሮው የዓለም የአካባቢ ቀን የፕላስቲክ ቆሻሻ ወደ ሥነ-ምህዳር እንዳይገባ መከላከል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ያተኩራል።
አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ምርቶችን በማስወገድ እና የፕላስቲክ ምርቶችን መልሶ መጠቀም የሚቻልባቸውን መንገዶች እንዲሁም ፕላስቲክ ያለሆኑ እና የአካባቢን ብክለት የማያስከትሉ ምርቶችን መጠቀም በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጎ ውይይት ይደረጋል።
የዘንድሮው የአካባቢ ጥበቃ የፕላስቲክ ብክለት ምን እንደሆነ፣ እንዴት ብክለቱ እንደሚከሰት እና ችግሩን ለመቅረፍ ምን ማድረግ ይገባል ለሚሉት 10 ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበት ነው።
- ምን ያክል የፕላስቲክ ቆሻሻ ይለቀቃል?
ተመራማሪዎች ከ1950ዎቹ ጀምሮ 9.2 ቢሊዮን ቶን የፕላስቲክ ቁሳቁስ መመረቱን፣ ከእነዚህ ውስጥ 7 ቢሊዮን ቶን የሚሆነው በቆሻሻ መልክ መወገዱን ጠቁመዋል።
- አካባቢን በመበከል ረገድ አደገኞቹ የትኞቹ የፕላስቲክ ዓይነቶች ናቸው?
እንደ የውሃ ጠርሙሶች፣ የእቃ ማጓጓዣዎች፣ የግብይት ቦርሳዎች፣ የሚጣሉ የፕላስቲክ ቁራጮች፣ የማቀዝቀዣ ከረጢቶች እና ማሸጊያዎች በከፍተኛ ደረጃ አካባቢን የሚበክሉት ናቸው።
- የፕላስቲክ ብክለት የሚበዛባቸው አካባቢዎች የት ናቸው?
ጥናቶች እንደሚያመላክቱት በምድራችን ላይ በፕላስቲክ ያልተበከለ አካባቢ የለም። ገጸ ምድር እና ከርሰ ምድር፣ ባሕሮች እና ውቅያኖሶች የፕላስቲክ ብክለት ሰለባዎች ሲሆኑ፣ ተመራማሪዎች ኤቨረስት ተራራ ላይ እንኳን የፕላስቲክ ቆሻሻ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።
- የፕላስቲክ ብክለት ለምን በጣም አሳሳቢ ሆነ?
የፕላስቲክ ቆሻሻ የአካባቢ ሥነ-ምህዳርን ይቀይራል። የፕላስቲክ ቆሻሻ የባሕር ነፍሳት የሚመገቡአቸው ዕፅዋት እንዳያድጉ በማድረግ የባሕር ውስጥ ሥነ-ምህዳርን ያዛባል፣ መሬት ውስጥ በመቀበር በተክሎች ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያደርጋል።
ፕላስቲክ "ማይክሮ ፕላስቲክ" ወደሚባሉ ጥቃቅን አካላት በመሰባበር ሰውነት ውስጥ የመግባት ባሕሪ አለው። እነዚህ የፕላሰቲክ ድቃቂዎች በጉበት ወስጥ፣ በእናት ጡት ወስጥ እና በወንድ የዘር ፍሬ ውስጥ ይገባሉ። በታሸገ አንድ ሊትር ውኃ ውስጥ 240 ሺህ ማይክሮ ፕላስቲኮች እንደሚገኙ በጥናት ተደርሶበታል።
ሌላው የፕላስቲክ ብክለትን አሳሳቢ የሚያደርገው ለአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑ ነው። የፕላስቲክ ቆሻሻ ለአየር ንብረት ለውጥ ከ3 በመቶ በላይ ድርሻ እንዳለው ጥናቶች ያመላክታሉ።
- ማይክሮፕላስቲክ ሰዎች ላይ ምን ተፅዕኖ ያደርጋል?
ማይክሮፕላስቲክ በሰዎች ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ አስመልክቶ እስካሁን በጥናት የተረጋገጠ ሰነድ ባይኖርም አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ታሳቢ ተደርጎ ሳይንቲስቶች ምርምራቸውን መቀጠላቸውን የተመድ አካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም መረጃ ያመላክታል።
- መልሶ መጠቀም ብቻ የፕላስቲክ ብክለትን ሊያስቀር ይችላል?
አብዛኛው የፕላስቲክ ምርቶች መልሶ ለመጠቀም በማያስችል መልኩ የሚመረቱ ሲሆን፣ መልሶ ለመጠቀም እንዲቻል የሚመረቱትም ቢሆኑ ከሁለት ጊዜ በላይ ጥቅም ላይ አይውሉም።
አብዛኛዎቹ ሀገራት ደግሞ የፕላስቲክ ምርቶችን መልሶ መጠቀም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂ የላቸውም። በአንጻሩ ደግሞ የፕላስቲክ ምርቶች በእጥፍ እየጨመሩ በመሆናቸው ፕላስቲክን መልሶ መጠቀም መቻል ብቻ በዚያ የሚመጣውን ብክለት አያስቀረውም።
- ስለዚህ ዓለም የፕላስቲክ ብክለትን እንዴት መቋቋም ትችላለች?
ዓለም በዚህ ጉዳይ ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለባት ይጠቀሳል። በተቻለ መጠን ፕላስቲክን መተካት የሚችሉ እና አካባቢን የማይበክሉ ምርቶችን መጠቀም፤ ፕላስቲክን መጠቀም አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት በሚችልበት መልኩ መሆን እንዳለበት ምክረ ሀሳብ እየቀረበ ነው። ለዚህ ደግሞ የሁሉም ትብብር ወሳኝ ነው።
- የፕላስቲክን ብክለት መቀነስ ውድ እና አስቸጋሪ ነው?
በአሁኑ ወቅት መንግሥታት እና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች የፕላስቲክ ብክለትን ለማስቀረት የሚያስችሉ ምርምሮችን እያበረታታቱ ይገኛሉ። ዓለም የፕላስቲክ ብከለትን መቀነስ ከቻለች 4.5 ትሪሊዮን ዶላር ማዳን እንምትችል በጥናት ተረጋግጧል።
- ዓለም የፕላስቲክ ብክለትን ለማስቀረት ምን እየሠራ ነው?
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የፕላስቲክ ብክለትን ለማስቀረት ሕጎችን አውጥተው ለመተግበር እየሞከሩ ናቸው። ችግሩ ድንበር ዘለል በመሆኑ ግን የሁሉንም የጋራ ትብብር ያስፈልጋል። ይህን ለማመቻቸትም ተመድ የተለያዩ ሀገራትን ያቀፈ ተደራዳሪ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሠራ ነው።
- የፕላስቲክ ብክለትን ማስቀረት በጣም አጣዳፊ የሚሆነው ለምንድነው?
የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ጥናት እንደሚያሳየው እ.አ.አ በ2060 የፕላስቲክ ቆሻሻ በዓመት በሦስት እጥፍ በማደግ ወደ አንድ ቢሊዮን ቶን እንደሚደርስ ይተነብያል። አሁን ያለው አዝማሚያ ከቀጠለ የፕላስቲክ ብክለት አሁን ካለው በእጥፍ በማደግ ምድር የምታበቅላቸው እፅዋት፣ ባሕር ያቀፈቻቸው ነፍሳት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ይገባሉ። ለዚህ ነው የፕላስቲክ ብክለትን ማስቀረት እጅግ አጣዳፊ የሚሆነው።
በለሚታደሰ