የትንሣኤ በዓል አዲስ ጅምርን፣ ተስፋን፣ እና ቤዛነትን ማሳያ እንደሆነ የክርስትና አስተምህሮ ያመለክታል።
ለክርስቲያኖች፣ ትንሣኤ የእምነታቸው ምሶሶ ነው። ትንሣኤ ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢአትና በሞት ላይ የተቀዳጀውን ድል የሚያመለክት ሲሆን፤ በእርሱ ለሚያምኑት የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ የሰጠም ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ህዝብ መዳን ቤዛ መሆኑ እንዲሁም ለአዲስ ሕይወት ማሳያ ከሙታን ሁሉ መሀል መነሳቱ በአማኞች ዘንድ እጅግ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው፤ ይህንንም ለማስታወስ ፋሲካን በተለያየ መልኩ ያከብሩታል።
በተለያዩ የዓለም ሀገራት የፋሲካ አከባበር ምን ይመስላል የሚለውን እናጋራችሁ፦
ትንሣኤ በሩስያ
ለሩስያውያን ትንሣኤ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ሃይማኖታዊ በዓል ነው። የበዓሉ የቤተክርስቲያን አገልግሎትም ከቅዳሜ ምሽት የሚጀምር እና እስከ እሑድ ጠዋት ድረስ የሚዘልቅ ነው። ትልልቆቹ የሩስያ አብያተ ክርስቲያናትም በዚህ ዕለት በክብረ በዓሉ ላይ በሚሳተፉ አማንያን ይሞላሉ።
ሩስያውያን ኦርቶዶክሶች ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተነሳ በማለትም ሰላምታ ይለዋወጣሉ። ለሰባት ሳምንታት ከፆሙም በኋላ፤ አይብ፣ የተቀቀለ እንቁላል እና ልዩ ዳቦ የትንሣኤ በዓል ዕለት የሚመገቧቸው ተወዳጅ ምግቦቻቸው ናቸው።
ትንሣኤ በሜክሲኮ
በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ሜክሲኮ በፋሲካ ዕለት የቤተክርስቲያን ደወሎች ይደወላሉ። ይህን ተከትሎም በየአብያተክርስቲያናቱ የክርስቶስን ትንሣኤ ለማክበር የፀሎት እና የዝማሬ ስርዓቶች በአማንያኑ ይከወናሉ።
ከቤተክርስቲያኑ የትንሣኤ አከባበር ሥነ-ሥርዓት በኋላ በየአካባቢው ነዋሪዎች ሰበሰብ ብለው በተለያየ መልኩ ቀኑን ያከብሩታል።
ሜክሲኮአውያን ከሆሳዕና ዕለት ጀምሮ የዘንባባ ጉንጉን በራሳቸው ላይ በማድረግ የበዓሉን ድባብ ይጀምሩታል።
ትንሣኤ በህንድ
በባህላዊና ሃይማኖታዊ ብዝሃነት በምትታወቀው ህንድ፣ የትንሣኤ በዓል ክርስቲያን ማህበረሰቦች በሚገኙባቸው በተለይም በኬረላ፣ በጎዋ እና በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በድምቀት ይከበራል። እያንዳንዱ አካባቢ በዓሉን ለየት ባለ መልኩ ያከብረዋል።
በጎዋ ፋሲካ በቀለማት ባሸበረቁ ድግሶች፣ በባህላዊ ምግቦች እና በስርዓተ አምልኮ ይከበራል። ብዙ ክርስትያን ነዋሪዎች ባሏት ኬረላ ግዛት ፋሲካ በምሽት ጸሎቶችና በቤተክርስቲያን አገልግሎቶች ይከበራል።
ትንሣኤ በአውሮፓ ሀገራት
በመላው አውሮፓ፣ የጎዳናዎችና አደባባዮች ድምቀት እና የመደብሮች መጨናነቅ የፋሲካ በዓል መዳረሱን ያሳያሉ።
በዓሉ ለአማኞች የቤተክርስቲያን አገልግሎቶች፣ ጸሎቶች እና የአምልኮ ሥርዓቶች በስፋት የሚከወኑበት ጊዜ ነው።
ታዲያ በዓሉ በባህል በተለመዱ ዓለማዊ ሁነቶችም ይከበራል። ለዚህ ማሳያ ከሚሆኑት መካከል በቅርጫት የተሞሉ እንቁላሎች በየቦታው መቀመጥ፣ ድግስና የከረሜላ እደላ ተጠቃሸ ናቸው።
አብዛኛው የአውሮፓ ሀገራት በዓሉን ቢያከብሩም፤ እያንዳንዳቸው የተለያየ ባህል እንዲሁም የራሳቸው የማክበሪያ መንገድ አላቸው።
ትንሣኤ በደቡብ አፍሪካ
በደቡብ አፍሪካ የትንሣኤ በዓል የክርስቶስን ስቅለት እና ትንሣኤ በሚያንጸባርቁ የአምልኮ ሥርዓቶች፣ ጸሎቶች፣ ዝማሬዎች እና ስብከቶች ይከበራል።
የፋሲካ ማግስት ወዳጅ ዘመዶች የሚሰበሰቡበት ቀን ሲሆን፤ ይህም አንድነትን እንዲያጠናክሩ እና የበዓሉን ጥልቅ ትርጉም እንዲያስቡ የሚረዳ የቤተሰብ ቀን በመባል ይታወቃል።
በዓሉን በባህላዊ ልብሶች አምረው እና ደምቀውም ነው ደቡብ አፍሪካውያን የሚያከብሩት።
ትንሣኤ በእስራኤል
በእስራኤል የሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሣኤ በዓልን በድምቀት ያከብራሉ።
በተለይም ስቅለትን የሚያከብሩት ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀሉን ተሸክሞ በተጓዘበት ጎዳና ላይ መስቀል በመሸከም እየተጓዙ ነው።
በትንሣኤው ዕለትም በጌቴ ሰማኒ ተገኝተው በፀሎት፣ በማስቀደስ እና በዝማሬ በዓሉን ያከብሩታል።
በሰለሞን ከበደ