ቀዳም ሥዑር:- የሰሙነ ሕማማት መጨረሻዋ ዕለት

ساعات 11 منذ
ቀዳም ሥዑር:- የሰሙነ ሕማማት መጨረሻዋ ዕለት

የሰሙነ ሕማማት መጨረሻዋ ዕለት ቅዳሜ ነች፡፡ በዚህች ዕለት ምዕመናን በጠዋቱ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ኪዳን አድርሰው ቄጠማ በራሳቸው አስረው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ በዚህ ዕለት የሚጾም ቢሆንም ስግደት አይሰገድም፤ መስቀልም መሳለም አይቻልም፡፡

የትንሣኤ ዋዜማ ቅዳሜ ከቀድሞው በተለየ መልኩ የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል "ቀዳም ሥዑር" ወይም የተሻረችው ቅዳሜ ትባላለች።

የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋው በመቃብር የዋለበት በመሆኑ ምእመናንም እንደ ሐዋርያት የትንሣኤውን ብርሃን ሳናይ እህል አንቀምስም በማለት በጾም ያሳልፏታል።

ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ ተላልፎ ከተሰጠበት ሐሙስ ሌሊት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው አልዞረም። ይመኩበት እና ተስፋ ያደርጉት የነበረው አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ሞቱን በማሰብ ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አሳልፈውታል።

ከሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረትም ሐዋርያት በማዘን፣ በመጾም እና በመጸለይ ዕለቷ እንዳከበሯት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንም ከሐሙስ ማታ ጀምረው የሚያከፍሉ /የሚጾሙ/ ለሁለት ቀን እህል ውኃ ሳይቀምሱ ያድራሉ፤ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ።

ይህ ማለት ክርስቶስ ወደ መቃብር በመውረዱ ከእህል ውሃ የማይጾምበት ሰንበት በጾም ተሻረች ለማለት እንጂ የቀዳሚትን ሰንበትነት የሚሽር እንዳልሆነ አባቶች ያስተምራሉ።

ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቄጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለሆነ "ለምለም ቅዳሜ" ትባላለች። ቄጤማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል።

ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል እያሰሙ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ (በመስቀሉ ሰላምን አደረገ) የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠ እና ትንሣኤውንም እንደገለጠ በማብሰር ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ። ምእመናኑም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ።

ቄጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፤ ይህም አይሁድ ክርስቶስን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሠሩበትን ድርጊት የሚያስታውስ ነው።

የቄጠማው አመጣጥ እና ምሥጢርም ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው። ምድር በጥፋት ውኃ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሠረችው ቄጠማ እና የወይራ ዝንጣፊ ይዛ በመምጣት ነው። ምሳሌውም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ኃጢአት ጠፋ፤ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነፃነት ታወጀ ለማለት ነው።

በሌላ አጠራር "ቅዱስ ቅዳሜ"ም ይባላል። ቅዱስ ቅዳሜ መባሉ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ሁሉ ያረፈበት ስለሆነ ነው።

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ የማዳን ሥራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፣ በነፍሱ ሲዖልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፤ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየ ዕለት ለማለት ቅዱስ ቅዳሜ እንደተባለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታስተምራለች።

በለሚ ታደሰ


ردود الفعل
Top