የጲላጦስ ሚስት አብሮቅላ ትባላለች፤ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ተሸክሞ እየወደቀ እየተነሣ ወደ ቀራንዮ በሚጓዝበት ጊዜ ጩኸት ግርግር ሰምታ ወጣች።
ኢየሱስ ክርስቶስ ፊቱ በደም ወዝ ተሸፍኖ ባየችው ጊዜ በፍጥነት እየሮጠች በመጎናጸፊያዋ (በሻሿ) ፊቱን አበሰችለት።
ይህ ትልቅ ሰማዕትነት ነው ይላሉ አባቶች፤ ምክንያቱም ጲላጦስ እንኳን ያልቻላቸውን ሕዝብ ሳትሳቀቅ ሳትፈራ ንግሥት ነኝ ብላ ሳትኮራ የፊቱን ወዝ አበሰችለት። ስለፍቅሯ እና ስለእምነቷ በመጎናጸፊያው ላይ የክርስቶስ መልኩ ታትሞ ቀርቷል።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ስሟ ተቀይሮ ቬሮኒካ (Veronica/ “ሠራጵታ”) ተብላለች። “ቬሮ ኢኮን” ማለት በላቲን ቋንቋ “የእውነት መልክ (ሥዕል) እውነተኛ ገጽ (ፊት)” ማለት ነው። ይህ ምሥል በአርመናውያን በቫቲካን እጅ ይገኛል።
እንደ ሃይማኖቱ አስተምህሮ ቬሮኒካ ሕልም በማየቷ ለባሏ ለጲላጦስ “በዚህች ሌሊት በሕልሜ በእርሱ ምክንያት ብዙ ስቃይ ሳይ አድሬአለሁና በዚህ ንፁህ ሰው ክፉ እንዳትሠራ ተጠንቀቅ” ስትል መልዕክት ልካበት ነበር። ይህ ነው አምላክነቱን እንድትረዳ ያደረጋት አንዱ ምክንያት ይላሉ የእምነቱ አባቶች።
የኢየሱስ ክርስቶስን ምሥለ ሥዕል ለመጀመሪያ ጊዜ የሣለው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ነው። የቬሮኒካ ምንም እንኳን ከዚህ ቢቀድምም ምሥለ ሥዕሉ በተዓምር የተገኘ እንጂ በሰው እጅ የተሣለ ስላልሆነ የመጀመሪያ የሚባለው የቅዱስ ዮሐንስ እንደሆነ ይታመናል።
ከ14-37 ዓ.ም በጊዜው የነገሠው ንጉሥ ጢባርዮስ ቄሳር ልጁ ታምሞበት ሲበሳጭ እና ሲጨነቅ ከቆየ በኋላ ልጁ ሞተበት። ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገውን ተዓምራት የሰማው ንጉሥ ክርስቶስ በተቀበረበት መቃብር ቦታ የልጁን በድን እና የምልጃ ደብዳቤ አድርጎ ልኮ ነበርና መልዕክተኞቹ የንጉሡን ልጅ በድን እና ደብዳቤውን በክርስቶስ መቃብር ላይ ሲያኑሩት በሕይወት ተነሣ።
ይህ ተዓምር ያስደነቀው ንጉሡም “የክርስቶስን እናት አምጡልኝ፤ እኔ ቋሚ ለጉአሚ አሽከር ሚስቴ ደንገጡር (ገረድ) ሆነን እናገለግላታለን” ቢል ሳይሳካለት ቀረ። እናም በዚህ ጊዜ ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ሔዶ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥዕል በዕለተ ዓርብ አይሁድ በመስቀል ላይ እንደሰቀሉት አድርገህ ሣልልኝ ብሎ ጠይቆታል። ዮሐንስም እሺ ብሎ ሣለለት።
የኢየሱስ ክርስቶስ የመግነዙ ጨርቅ ዮሐንስ ወንጌላዊ እና ጴጥሮስ በባዶው መቃብር ውስጥ ገብተው ያዩት ጌታ ተገንዞበት የነበረውን ሰበን እና መጠምጠሚያ ላይ የጌታ አካል ታትሞ ነበር። ይህ መግነዝ ጨርቅ በሮም ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ በጣሊያን ቱሪን ከተማ በሚገኘው በዚህ መግነዝ ላይ ያለው ሥዕል ቁመቱ 5 ጫማ ከ 11 ኢንች የሆነ ነው፤ ያረፈ ወይም ያንቀላፋ የሚመሰል፣ እጆቹ በወገቡ ላይ ዘና ብለው ተዘርግተው ሁለቱ እግሮቹም በቁርጭምጭሚቱ ላይ ተደራርበው እንዳለ የሚያሳይ ሥዕል ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ በተገለጸው የዕብራውያን ልማድ መሠረትም በሥዕሉ ላይ ፀጉሩ ተጎንጉኖ ይታያል። በወንጌሉ ውስጥ በተገለጠው ሁኔታ በመገረፉ እና በመቸንከሩ ምክንያት ቁስል እና ሰንበር በፊቱ እና በሌላው የአካል ክፍሉ ላይ ይታይበታል። ይህም በወንጌል ውስጥ በተገለጠው የመገረፍ፣ የመደብደብ እና የመቸንከር ሁኔታውን በትክክል ይመስላል።
ሁለቱ ትከሻዎቹ ከባድ መስቀል እነደተሸከመባቸው የሚየሳዩ ምልክቶች ይታይባቸዋል። እጆቹ እና እግሮቹም እንደተቸነከሩ የሚያሳይ ምልክት ይታይባቸዋል። የጎን አጥንቱ መካከል ያለው ቦታም በጦር ተወግቶ እንደ ቆሰለ ያሳያል። ይህ በመግነዙ የሚታየው ምልክት ነው።
የኢየሱስ ክርስቶስን ምሥለ ሥዕል በተመለከተ ዛሬም ድረስ ሰፊ ምርምር የሚደረግበት ነው። በተለይ በመግነዙ ላይ የሚታየው ምሥል በእርግጥም በተዓምር የተገኘ ወይስ የተሣለ ሥዕል የሚለውን ለማወቅ ብዙ ዓመታት የዘርፉ ተመራማሪዎች ብዙ ጥናቶችን አድርገዋል።
እናም በእጅ ወይም በወቅቱ በነበሩ ቴክኖሎጂዎች ያልተሠራ መሆኑን ቢያረጋግጡም ዛሬም ድረስ የቬሮኒካ መጎናጸፊያ (ሻሽ) እና የኢየሱስ ክርስቶስ መግነዝ ላይ ያለው ምሥለ ሥዕል ምርምር ይደረግባቸዋል።
ይህን ጽጹፍ ለማዘጋጀት አምደ ሃይማኖት በብርሃኑ ጐበና፤ ቅዱሳን ሥዕላት በሚሊዮን በለጠ እንዲሁም ወንጌል ቅዱስ ንባቡ እና ትርጓሜው፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መጻሕፍትን ተጠቅመናል።