ተሞክሮ አንድ፣
ለብዝሃ የኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት በመስጠትና በፅናት የታገዘ እልህ አስጨራሽ ርብርብ በማድረግ በአንድ ትውልድ የጊዜ ምዕራፍ ውስጥ ብቻ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት መዝገብ የሚቻል መሆኑን ከቬየትናም የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ መረዳት ይቻላል፡፡ ቬየትናሞች ለግብርና ልማት፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ለቱሪዝም፣ ለሰው ሃብት ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት እንዲሁም የነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነቶችን በማድረግ የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ስበዋል፤ በዚሁ ባለፉት 30 ዓመታት ከ5-7 በመቶ ያልተቋረጠ እድገት በማስመዝገብ አስደናቂ የኢኮኖሚ እድገትን አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ሁኔታ በተለይም ከለውጡ ወዲህ በአንድ ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ከተንጠለጠለ የኢኮኖሚ ግንባታ ወደ ብዝሃ ሴክተር የኢኮኖሚ ግንባታ ተሸጋግራለች፡፡ በአገር በቀል የኢኮኖሚ እቅዷና ሪፎርሟ ግብርናን፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ለዲጂታል ኢኮኖሚ የኢኮኖሚ ግንባታዋ አዕማድ ወይም ምሳሶ በማድረግ ባለፉት 7 ተከታታይ ዓመታት ከሰባት በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት በማረጋገጥ ታሪካዊ ስራ አከናውናለች፡፡ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷንም በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በእጥፍ አሳድጋለች፡፡
የቬየትናሞቹ ልምድና ተሞክሮም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግንባታ አቅጣጫ ትክክለኛነትን በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከቬየትናም የተገኘው ልምድና ተሞክሮ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሪፎርም በማጠናከርና ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር በያዘችው መንገድ ከቀጠለች በአጭር ጊዜ ውስጥ ቬየትናም ካስመዘገበችው የኢኮኖሚ እድገት የላቀ እድገት ማስመዝገብ እንደምትችል የሚጠቁም ነው፡፡
ተሞክሮ ሁለት፣
ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ የቬየትናም ዜጎች በ1990ዎቹ ዓመታት ከድህነት ወለል በታች ይኖሩ ነበር። ሆኖም ቬየትናም በተከተለችው የኢኮኖሚ ዕድገት አቅጣጫ በተለይም ለግብርና ልማት በሰጠቸው ልዩ ትኩረት በ2020 ይህን አኃዝ ወደ 4% (በመቶ) ዝቅ እንዲል አድርጋለች:: የግብርና ሪፎርሟ ውጤታማ በመሆኑ ራሷን በምግብ ሰብል ከመቻል አልፋ በሩዝ፣ በፍራፍሬ፣ በቡና እና ሌሎች የግብርና ምርቶች በቀጣናው ከፍተኛ ላኪ ሀገር ሆናለች::
ይህ በጎ ልምድና ተሞክሮም፣ ኢትዮጵያ ተረጅነትን በመቀነስ፣ ራስን በምግብ ሰብል በመቻል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እያደረገችው ላለው ሁለንተናዊ ጥረት በእጅጉ ጠቃሚ አስረጂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በግብርና ልማት በተለይም በስንዴ አብዮት ራስን ለመቻል ያደረገችው እንቅስቃሴ ስኬታማ ሆኗል፡፡ ከዚህ የተገኘውን ልምድ በመውሰድ አሁን ደግሞ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በሩዝ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ጀምራለች፡፡ በዚህም ረገድ የቬየትናሞች ስኬት ኢትዮጵያ በትክክለኛ አቅጣጫ እየተጓዘች መሆኗን ከማረጋገጥ ባለፈ ጠቃሚ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡
በመሆኑም የጀመርናቸውን መልካም ስራዎች የሚያጠናክሩ የአገር ውስጥ ልምዶችን ከማጎልበት ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታዩ በጎ ልምዶች በመቀመር በግብርና ዘርፍ የተጀመረውን መነሳሳት ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ እንደ ቬየትናም ያሉ በግብርና ልማት ስራዎች ውጤታማ የሆኑ አገሮች ኢትዮጵያ ለምትካሂዳቸው የሪፎርም ስራዎች ጥሩ መነሻ ሆኖ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
ተሞክሮ ሶስት፣
ቬየትናም የዓለም ንግድ ድርጅትን ጨምሮ በቀጠናው ካሉ አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ድርጅቶች ጋር በነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ዙሪያ ሰፋፊ ድርድሮችን አካሂዳለች፡፡ በዚህም ረገድ ውጤታማ ሆናለች፡፡ በየዓመቱ ከ34 ቢሊየን ዶላር በላይ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች፡፡ በተለይም እንደ ኤሌክትሮኒክስ፣ ጨርቃጨርቅና የጫማ አምራች ኢንዱስትሪዎችን መሳብ ችላለች፡፡ ይህም በቀጠናው ከፍተኛ የሚባል የኢንቨስትመን ስበት ማሳያ ነዉ፡፡
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት ጋር ብዙ ርቀት የተጓዘ ድርድሮችን በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡ ድርድሮቹም ውጤት እየተገኘባቸው መጥቷል፡፡ በምስራቅ አፍሪካም ነፃ የንግድ ስምምነት ለመፍጠር ከሀገሮቹ ጋር በርካታ ድርጅሮችን እያካሄደች ነው፡፡ ይህም ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡
በአፍሪካ ህብረት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካትም ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ስራ እያከናወነች ነው፡፡ ነፃ የንግድ ቀጠና ድርድር በማካሄድ ቬየትናምን ሰፊና ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንድታገኝ ያስቻሏትን የድርድር መንገዶች፣ አሰራሮችና የህግ ማዕቀፎችን በመመርመር ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ሁኔታ ለምትፈጽማቸው ስራዎች እንደየሁኔታው መጠቀም ይገባል፡፡
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የቬየትናም የአምራች ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ታሪፍ እየተጋረጠባቸው መጥቷል፡፡ በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ታሪፍ፣ ታዳሽ የሃይል አቅርቦት፣ ርካሽ ጉልበት፣ እየዘመነ የመጣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በአንድ ማዕከል ወይም አካባቢ የተሰበሰቡ ኢንዲስትሪዎች መጠናከር እና የነጻ የንግድ እና ኢኮኖሚ ዞኖች መፈጠር እንደ ቬየትናም ላሉ ሀገሮችና ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትራችን ጉብኝት ከዚህ አኳያ ጥሩ ልምድ ለመቅሰም ብቻ ሳይሆን ባለሀብቶቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም መንገድ የከፈተ ነው፡፡ ይህን ምቹ እድል አጠናክሮ መጠቀም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
ተሞክሮ አራት፣
ቬየትናሞች ለሰብአዊ ልማት በተለይም ደግሞ ለቴክኒክና ሙያ የሰጡት ልዩ ትኩረት ኢኮኖሚያቸው ይበልጥ እንዲያድግ ረድቷል:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ንጥር ቅባለቸው ከ99 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ንጥር ቅበላውም ወደ ዘጠና በመቶ የተጠጋ ነው፡፡ ይህ አሃዝ በመካከለኛ እድገት ደረጃ ካሉት ሀገሮች ከፍተኛው ነው፡፡ ቬየትናም በዓለም አቀፉ የሰብአዊ ልማት index መሰረት ከሲንጋፖር ቀጥላ ሁለተኛዋ የሰብአዊ ካፒታል የገነባች ሀገር ሆናለች፡፡
ኢትዮጵያም በቅርቡ ለመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ የትውልድ ግንባታ አቅጣጫን ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የቬየትናም ጉብኝትም ከዚህ አኳያ ጠቃሚ ልምድ የተገኘበት ነው፡፡ ቬየትናሞች የኢትዮጵያን ሰብዓዊ ሀብት ልማት ለማገዝ ቃል ገብተዋል፡፡ በየዓመቱ መጠነኛ ቁጥር ላላቸው የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ስኮላርሺፕ ለመስጠት እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) አብሮ ለመስራት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ይህንኑም በአግባቡ መጠቀም ያስፈልገናል፡፡
በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቬየትናም የነበራቸው ቆይታ ስኬታማና የኢትዮጵያን አስፈላጊ አጋርነት ያረጋገጠ ነው። የልዑኩም ቆይታ የኢትዮጵያን ያለፉት 7 የለውጥ ዓመታት ተሞክሮ ለመቃኘትና የጉዞአችንን ትክክለኛነት ከማረጋገጥ ባለፈ መጪው ጊዜ አዲስ የታሪክ እጥፋት የምናስመዘግብበት እንዲሆን አቅም የፈጠረ ነው።
በቬየትናም የቆይታ ምዕራፍ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የታደሙበት “ዘላቂ እና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የቬየትናሙ የፒ4ጂ ጉባኤ፣ ትርጉም ያለው ውጤት የሚያስገኙና ትልቅ አቅም ያላቸው ፕሮጀክቶች የታዩበት መሆኑ ታይቷል። የአረንጓዴ ልማት እድገትን ለማፋጠን፣ አዳዲስ አጋርነቶችን ለማጎልበት እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ለሚደረገው የጋራ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትራችን በመልዕክታቸው አስገንዝበዋል።
ጉባኤው ለ2027 ለሀገራችን ሌላ እድል አምጥቶና የመሪያችንንና ህዝባችንን ክብር ባረጋገጠ አኳሃን ኢትዮጵያ 5ኛውን የፒ4ጂ ጉባኤ እንድታካሂድ ችቦ አረካክቧል። በመሆኑም ሀገራችን እንደ ቬየትናም በሌላ ምዕራፍ ልምድና ተሞክሮዋን፣ በብዝሃ እምርታና ስኬት ይዛ እንድትቀርብ ለማድረግ ርብርባችንን ከወዲሁ አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል።