“በዱቤ ወደ ውጭ ሀገር እንልካለን” በሚል በተለያዩ ታዋቂ ሰዎች፣ አርቲስቶች እና ቲክቶከሮች ማስታወቂያ የተታለሉት

منذ 3 أيام
“በዱቤ ወደ ውጭ ሀገር እንልካለን” በሚል በተለያዩ ታዋቂ ሰዎች፣ አርቲስቶች እና ቲክቶከሮች ማስታወቂያ የተታለሉት

በኢትዮጵያ በርካታ ተቋማት ሕጋዊ ፈቃድ ወስደው ወደ ተለያዩ ሀገራት የሥራ ስምሪት ላይ እየሠሩ ይገኛሉ። በዚያው ልክ ግን “ዜጎችን ወደ ውጭ እንልካለን” በሚል ስም ገንዘብ ሰብስበው አድራሻ የሚቀይሩ እንዳሉ በተደጋጋሚ የሚሰማ ጉዳይ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ “ወደ ውጭ ሀገራት እንልካለን በሚሉ ተቋማት ተጭበርብረናል” የሚሉ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮች ቅሬታዎቻቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።

ወጣት ተመስገን ሰለሞን ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆን “AIM ULTRA CONSULTANCY” በተባለ ድርጅት ደርሶብኛል ስላለው በደል ለኢቢሲ ዶትስትሪም በዝርዝር ተናግሯል።

እሱ እንደሚለው “በዱቤ ወደ ውጭ ሀገር እንልካለን” በሚል በተለያዩ ታዋቂ ሰዎች፣ አርቲስቶች እና ቲክቶከሮች የሚነገረውን የድርጅቱን ማስታወቂያ በመመልከት ሂደቱን ጀመረ።

ሂደቱን በሚጀመርበት ጊዜም ‘በዱቤ’ በሚል የተዋወቀው ነገር ቀርቶ ‘ለተለያየ ሥራ ማስኬጃ’ በሚል ክፍያዎችን ተጠይቆ ከፍሏል። በዚህ ድርጅት እሱን ጨምሮ ከ56 ሺህ እስከ 700 ሺህ ብር የተጭበረበሩ ሰዎች እንዳሉ ነግሮናል።

የድርጅቱ ባለቤት “ቤተልሔም ታደሰ” እንደምትባል እና “ጉዳያችሁን አስጨርስላችኋለው፤ በእኔ ላይ ጣሉት” በማለት በተደጋጋሚ የኤምባሲ እና ተያያዥ ክፍያዎችን እንዳስከፈለቻቸው፣ እሱም መተዳደሪያው የነበረችውን ባጃጅ ሽጦ እና የቤተሰቡን መሬት አስይዞ በመበደር የተጠየቀውን ቀሪ ክፍያ መፈጸሙን ነው የነገረን።

ሂደቱን ከጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ ሁሉም ነገር አልቆ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም ከሀገር ትወጣላችሁ ስለተባለ ከሚኖርበት አካባቢ ቤተሰቦቹን ተሰናብቶ ወደ አዲስ አባባ ይመጣል።

ሆኖም እንዳሰበው ያልሆነለት ወጣት ተመስገን ተጨማሪ 250 ሺህ ብር እንዲከፍል ይነገረዋል።

ያለውን ነገር ሁሉ ሸጦ እና የቤተሰብን መሬት አስይዞ አንደተበደረ እና አሁን ተጨማሪ ብር መክፈል እንደማይችል ይነግራቸዋል።

ነገር ግን “ተጨማሪ ካልከፈልክ አትሄድም” ይሉታል፤ ይህን የሰማው ተመስገን "ወይ ብሬን መልሱ ወይ ወደ ውጭ ላኩኝ" ይላቸዋል።

በስምምነታቸው መሠረት በመካከላቸው አለመግባበባት ከተፈጠረ የተከፈለው ብር በ3 ወር ውስጥ ተመላሽ እንዲሆን  ያስገድዳል። “ብርህ ይመለስልኻል፤ ጠበቅ” የተባለው ተመስገን ገንዘቡን ሊመልሱለት ቀርቶ አድራሻቸውን ቀይረው ጠፉበት።

ቤተሰቦቹን ተሰናብቶ የመጣው ይህ ወጣት ወደ ቤተሰቦቹ መመለስ እንዳልቻለ ነው የነገረን። እንደ እሱ ሁሉ ብዙ ወጣቶች ተስፋ ሰንቀው ቤተሰባቸውን ተሰናብተው ከክልል ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ቢመጡም ያሰቡት ሳይሳካ በተቃራኒው ጎዳና ለመውጣት መገደዳቸውን ጭምር ነው የነገረን።

ጥላሁን ሙላት ሌላኛው የዚህ ጉዳይ ሰለባ ሲሆን፣ “AIM ULTRA CONSULTANCY” በሚባለው ድርጅት 450 ሺህ ብር ተጭበርብሬያለው ይላል።

የጉዞ ሂደቱን የዛሬ 4 ዓመት እንደጀመረ የሚናገረው ይህ ወጣት ወደ ሮማኒያ ትሄዳላችሁ ከተባሉት ሰዎች መካከል አንዱ እንደነበር ያስታውሳል። እሱ እንደ ነገረን፣ ከጉዞው በተጨማሪ የጤና ምርመራ፣ የትራንስፖርት፣ የሥራ ሥልጠናዎች በየጊዜው ያደርጉ ነበር።

በዚህ ጉዳይ  ላይ አስተያየታቸውን የሰጡን ቅሬታ አቅራቢዎች የተቋሙ ቢሮ አራት ኪሎ በሚገኘው አምባሳደር ሞል ላይ መሆኑን ጠቁመውን ስለነበር  ኢቢሲ ዶት ስትሪም በስፍራው ተገኝቶ ተቋሙ አለመኖሩን አረጋግጧል።

እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ መረጃ ከሆነ ድርጅቱ እንዲህ ያለ ሥራ ከሰራ በኋላ አድራሻውን እንደቀየር ነው የነገሩን።

ጌታሁን በላይ ሌላኛው ተመሳሳይ ቅሬታ ያለው ወጣት ሲሆን “ባየኋቸው የሚማርኩ እና ሳቢ ማስታወቂያዎች ተታልያለሁ” ይላል።

"ከምንም በላይ ይህን ድርጅት እንድመርጥ ያደረገኝ ደግሞ በሰዓቱ በአንዴ ሙሉ ክፍያ ከፍዬ የምሄድበት አቅሙ ስላልነበረኝ እናም እነሱ ጋር በዱቤ በመሆኑ ነበር” ሲልም አስታውሷል።

“ከ10% እስከ 25% ቅድመ ክፍያ ብቻ ከፍለው ቀሪውን የሚሄዱበት አገር እየሰሩ ይከፍላሉ" በመባሉ በ25% ቪአይፒ አማራጭ 167 ሺህ ሃምሣ ብር ከፍሎ ውል መዋዋሉን ነው የነገረን።

ነገርን ግን በተደጋጋሚ ለተለያየ ጉዳይ ብር በመጠየቃቸው ከተለያዩ ሰዎች ተበድሮ ወደ 600 ሺህ ብር መክፈሉን እና በኋላ ላይም ነገሩ የውኃ ሽታ ሆኖ መቅረቱን በቁጭት ገልጿል።

የነበራትን የግል ሥራ በመዝጋት ለዚህ የውጭ ጉዞ ሂደት የከፈለችው ደግሞ ወ/ሮ ሳባ ተክላይ  አሁን ላይ ሥራ አጥ እንደሆነች ትናገራለች።

የግል የእንጨት ቤት የነበረው ማስረሻ አለበል የተባለው ተበዳይ ደግሞ ጉዞውን ለማድረግ ሠራተኞችን በትኖ እና ማሽኖችን ሸጦ የተጠየቀውን ክፍያ ቢፈጽምም ጭራሽ ያለውን ሁሉ ለማጣት ተገድዷል።

ኢቢሲ ዶት ስትሪም ይህ “AIM ULTRA CONSULTANCY” የተባለው እና በዚህ ልክ ቅሬታ የቀረበበት ተቋም ሕጋዊ እውቅና እና የውጭ ሥራ ስምሪት ፍቃድ ያለው ስለመሆኑ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን ጠይቋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ “AIM ULTRA CONSULTANCY” በሚል ስም ለሚሠራ ተቋም የሰጠው የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ፍቃድ አለመኖሩን የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አበበ ዓለሙ ገልጸውልናል።

ቅሬታው የቀረበበት “AIM ULTRA CONSULTANCY” ጉዳዩን በተመለከተ አስተያየቱን ለማካተት ወደ ተቋሙ በተደጋጋሚ በመደወል ሐሳብ እንዲሰጡን ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ የተቋሙን ኃላፊም ሆነ ተወካይ ሐሳብ ለመቀበል ኢቢሲ ዝግጁ ነው።

በሜሮን ንብረት


ردود الفعل
Top