የኢትዮጵያ የግብርና ሪፎርም የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ለምናደርገው ጥረት አርዓያ ነው፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

1 Mon Ago 298
የኢትዮጵያ የግብርና ሪፎርም የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ለምናደርገው ጥረት አርዓያ ነው፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሦስተኛ ቀኑን በያዘው "ከረሃብ ነጻ ዓለም" ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ምርታማነትን የሚጨምር የግብና ሪፎርም መተግበሯን ገልጸዋል፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ በግብርና ላይ ያደረገችው ሪፎርም ድርቅን የሚቋቋሙ ሰብሎችን በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ ማምረት ያስቻላት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
 
አግሮ ኢንዱስትሪ ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ታምርት እንቅስቃሴም ግብርናውን ወደ ቀጣይ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቁን ድርሻ እየተወጣ እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡
 
ረሃብ አንድ ብቻውን የቆመ አጀንዳ ስላልሆነ የሁላችንም እጅ በእጅ መያያዝ ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን፣ ድርቅን የሚቋቋሙ ሰብሎችን በመጠቀም እና የልምድ ልውውጥ በማድረግ መቋቋም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
 
ሀገራት በፖሊሲያቸው መናበብ እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ዓለም አቀፍ ተቋማትም በዝቅተኛ ደረጃ ያሉ አርሶ አደሮችን እንዲደግፉ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡
 
አክለውም በግብርናው ዘርፍ ድንበር ተሻጋሪ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሊኖር እንደሚገባ ገልጸው ይህንንም ዓለም አቀፍ ተቋማት ትኩረት ሰጥተው ሊደግፉት እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
 
እጅ ለእጅ ከተያያዝን ዓለምን ከረሃብ ነጻ በማድረግ ክብራችንን መጠበቅ እንችላለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
 
በለሚ ታደሰ

Feedback
Top