ዳያስፖራው እና ፐብሊክ ዲፕሎማሲው ለኢትዮጵያ መብትና ብሔራዊ ጥቅም

21 Hrs Ago 389
ዳያስፖራው እና ፐብሊክ ዲፕሎማሲው ለኢትዮጵያ መብትና ብሔራዊ ጥቅም

በኢትዮጵያ ከ4 ዓመታት በፊት የተካሄደው ሪፎርም ትውልደ ኢትየጵያውያን በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እድል የከፈተ ነበር።

ከ35 ዓመታት በላይ በስዊድን ሀገር የኖሩት ትውልድ ኢትዮጵያዊው አቶ ያሲን አህመድም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።

ጠቅላይ ሚንሰትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ከሀገራቸው ውጭ የሚኖሩ ትውልድ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ የሚያደርጉበት እድል ጠባብ እንደነበር ነው የሚያነሱት አቶ ያሲን አህመድ።

መንግስት የዲፕሎማሲ ስራውን መስራት አንዱ ሃላፊነቱ ቢሆንም አብዛኛውን ስራ ይሰራ የነበረው በኦፊሻል ዲፕሎማሲ ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከ4 ዓመት በፊት ሌላ አዲስ መንገድ በመከፈቱ የ“የኢትዮጵያ የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ ተቋም” በማቋቋም በአረብኛ ቋንቋ ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ወቅታዊ መረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበሰረብ በመስጠት ላይ መሆናቸውን በተለይም ለኢቢሲ ሳይበር ገልፀዋል፡፡

አቶ ያሲን በሚኖሩበት በስዊድን ሀገር ውስጥ የጀርመን፣  እንግሊዝ እና አሜሪካ  ዜጎች ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችን መስርተው ለሀገራቸው ብሄራዊ ጥቅም መከበር ሌት ተቀን እንደሚሰሩም በተሞክሮነት አንስተዋል።

ማኅበራዊ ሚድያን በመጠቀም "የኢትየጵያ የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ ተቋምም" ኢትዮጵያን ለማያውቁ አውሮፓውያንና የአረቡ ዓለም ዜጎች ሀገርን የማስተዋወቅ፣ ብሄራዊ ጥቅምን የመጠበቅ ስራ እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በአውሮፓና በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩና አረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን  እርስ በእርሳቸው ተገናኝተው  የሀሳብ ልውውጥ ማድረግ የሚችሉበት ኔትዎርክ መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል።

ግብፅ በኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገሮች ውስጥ በግልፅም ሆነ በድብቅ  እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ በመከታተል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንተስዋል፡፡

ሶማሊያ በአልሸባብ ስትታመስ፤ በድርቅ ስትጠቃ አንድም ድጋፍ ሳታደርግ የቆየችው ግብፅ አሁን ለሶማሊያ ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጓ በኢትዮጵያ በእጅ አዙር ጉዳት ለማድረስ ፅኑ ፍላጎት እንዳላት ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በአንፃሩ የሰላም አስከባሪ ወደ ሶማሊያ በማላክ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ገንቢ ሚና መጫወት ችላለችም ብለዋል፡፡

 

በላሉ ኢታላ


Feedback
Top