ማርሽ ቀያሪው - ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር

1 Mon Ago 463
ማርሽ ቀያሪው - ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር

የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓለማ በዓለም አደባባይ በክብር ከፍ ያደረገ፣ የድል ብሥራትን ካፅናፍ አፅናፍ ያስተጋባ፣ የኢትዮጵያውያን የምንጊዜም ጀግና፣ የመጪው ትውልድ ፅኑ አብነት፡፡

በላባቸው የሚያስከብሯት ዕንቁ ልጆች የማታጣው ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል ያገኘችው ማርሽ ቀያሪውም ታሪኳን በወርቅ ቀለም ጻፈላት፡፡ አበበ ቢቂላ አርአያው እንደሆነ የሚገልጸው ይህ ጀግና፣ በሞስኮ ኦሎምፒክ በ5 እና 10 ሺህ ሜትሮች ድርብ ወርቅ በማሸነፍ የመጀመሪያው አፍሪካዊ በመሆን የአበበን ታሪክ ደገመ፡፡

ለኢትዮጵያ ያለው ፍቅር ፅኑ በመሆኑ በዘመኑ ብዙ ዋጋም ከፍሎበታል፤ ይሁን እንጂ ከከፍታው ሳይወርድ ላመነበት አቋም ኖሮ አልፏል፡፡

በሞንትሪል ኦሎምፒክ ላይ በመሳተፍ ዓለምን ያስደምማል ተብሎ የተጠበቀው ሻምበል ምሩፅ፤ ኢትዮጵያ የአፓርታይድ ሥርዓት በደቡብ አፍሪካ ላይ ሲያደርስ የነበረውን የዘር መድልዎን በመቃወም ውድድሩን ስላቋረጠች ሳይወዳደር ቀረ፡፡ እሱም ወቅቱን ሲያስታውስ "ያ ውሳኔ ለምድሪቱ ሰብዓውያን ሁሉ እኩልነት ሲባል የተከፈለ ታላቅ ዋጋ ነበር" ብሏል፡፡

በውድድሩ ተሳትፎ የድል ሜዳሊያዎቹን ለራሱ እና ለሀገሩ ሊያስገኝ ጓጉቶ የነበረ ቢሆንም ሀገሩ በወሰነችው ውሳኔ ምክንያት ምኞቱ ሳይሳካ ቢቀርም ግን ቅር አልተሰኘም፡፡ ብዙዎች ይህንን አስታክከው በዚያው እንዲቀር ሊያግባቡት ቢሞክሩም ምሩፅ ግን ወደሚወዳት ሀገሩ መመለስን መረጠ፡፡

ለምን ያንን ውሳኔ እንደወሰነ ሲጠየቅም፣ "ሀገሬን እወዳታለሁ፤ ሀገሬን ማንም ከእኔ ሊያርቃት አይችልም፤ እኔ በሀገሬ የምኮራ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ሀገሬ በአፓርታይድ የዘር መድልዎ ላይ የወሰደችው አቋም የእኔም የግሌ አቋም ነው፤ ያን አቋም በመያዜም እጅግ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል፤ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሰው ልጆች ነፃነት እና እኩልነት አምናለሁ" በማለት ነበር የመለሰው፡፡

ሻምበል ምሩፅ በ1972 የሚዩኒክ ኦሎምፕክ የወርቅ ሜዳሊያ አገኝበታለሁ ብሎ የተዘጋጀበት ርቀት 5 ሺህ ሜትር የነበረ ቢሆንም፣ ብዙም ባልተዘጋጀበት 10 ሺህ ሜትር ተወዳድሮ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም በአሰልጣኞቹ በኩል በተፈጠረ መዘግየት ወደ መወዳደሪያ ሜዳው ሲደርሱ የ5 ሺህ ሜትር ውድድር ተጀምሮ ስለነበር እንደሆነ ራሱ ተናግሯል፡፡

የሱ ጥፋት ባልሆነ ምክንያት የነሀስ ሜዳሊያ ይዞ ወደ ሀገሩ ሲመለስ ግን የጠበቀው እንኳን ደህና መጣህ፤ በቀጣይ ቁጭትህ ትወጣለህ የሚል አቀባባል ሳይሆን እስር ነበር፡፡ ከሚዩኒክ መልስ ለ8 ወራት ታሠረ፡፡ ከወህኒ ተፈቶ ታሪክ እንደሚሠራ ያመነው ምሩፅ  ከማረሚያ ቤት ፖሊሶች ጋር በጧት እየተነሳ ጠንካራ ልምምዱን ቀጠለ፡፡ በሚዩኒኩ ኦሎምፒክ በ5 ሺህ ሜትር ያልተወዳደረው ያኔ የነበረውን የደርግ መንግሥት በመቃወም ነው ብለው በማመን ወደ ወህኒ የወረወሩት የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪዎችም በውድድሩ ያልተሳተፈው በአሰልጣኞች ስህተት መሆኑን ሲረዱ ከወህኒ ቤት ፈቱት፡፡

እዚህ ጋር ምሩፅ በሀሰት ተከሶ ለእስር ከዳረገው ውንጀላ ነጻ እንዲሆን የወቅቱ የአየር ኃይል አዛዥ ጄኔራል ፋንታ በላይ ትልቁን ሚና እንደተጫወቱ በአንድ ወቅት ከኢቲቪ ጋር ባደረገው ቆይታ ሲገልጽ፣ "አየር ኃይል ታስሬ እያለሁ ወደ ማዕከላዊ ዕዝ እንድዘዋወር ተወስኖ ነበር፤ ነገር ግን ጄኔራል ፋንታ በላይ ቆይ እስቲ ነገሩ ይጣራ፤ ይህ ሰውዬ የታሰረው በአጉል ጥርጣሬ ሊሆን ስለሚችል ሳናጣራ አንልክም ብለው ስንት ተከራክረው ነጻ አወጡኝ፤ እንደዚያ እሳቸው ባይደርሱልኝ ኖሮ ሌላ እርምጃ ይወሰድብኝ ነበር" ብሏል፡፡

በናይጄሪያዋ ሌጎስ በተደረገው የመላ አፍሪካ ሻምፒዮና በ10 ሺህ የወርቅ፣ በ5 ሺህ ደግሞ የብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት ስሙን አድሶ ሀገሩንም ከፍ አደረገ፤ ራሱንም ከአጉል ጥርጣሬ ነጻ አደረገ፡፡

የራሱንም የሀገሩንም ታሪክ በወርቅ ቀለም የጻፈበት የ1980ው የሞስኮ ኦሎምፒክ ደረሰ፡፡ በሞስኮ አሎምፒክ እስካሁን ድረስ ዓለም ሁሉ ባስታወሰው ቁጥር የሚታወስበትን "ማርሽ ቀያሪው (Yifter the Shifter)” የሚል ቅፅል ያገኘበት ሆኖ በታሪክ መዝገብ ላይ ሰፈረ፡፡ በውድድሩ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሳይጠበቅ ተምዘግዝጎ በመውጣት ያሸነፈበት አስገራሚ ብቃቱ ነበር ያን ስም ያሰጠው፡፡

በዚያ ውድድር በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ ሜትሮች ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ አስጠራ፤ ሰንደቋንም ከፍ አደረገ፡፡ እሱ በሌለበት የሞንትሪያል ኦሎምፒክ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ በሞስኮም ያንን ታሪክ በመድገም ከሩጫው ለመሰናበት ተዘጋጅቶ የመጣውን ፊንላንዳዊ አትሌት ሌስ ቬርን በማሸነፍ ለሀገሩ እና ለአፍሪካ የመጀመሪያውን ድርብ ወርቅ አመጣ፡፡ ከምንጊዜም የኦሎምፒክ ጀግኖች እና ክስተቶች መካከልም ስሙን አስመዘገበ፡፡ ያ ወደ ጎልማሳነት ዕድሜ የተጠጋ በመሰለው አቋሙ ያሳየው አስገራሚ ብቃቱም "ከሌላ ፕላኔት የመጣ አይበገሬ አትሌት" ተብሎ እንዲጠራም አድርጎታል፡፡

ለሞስኮ ውድድር ሲዘጋጅ ዕድሜው ተፅዕኖ ያደርግበት ከሆነ ብለው ሲወዛገቡ ላስተዋላቸው ጋዜጠኞች፣ "ሰዎች ዶሮዎቼን ሊሠርቁኝ ይችላሉ፣ ሰዎች በጎቼን ሊሠርቁኝ ይችላሉ፣ ያ ችግር የለውም፣ ዕድሜዬን ግን ማንም ሰው ሊሠርቀኝ አይችልም፤ ከዕድሜዬ ይልቅ ስለ አስደናቂው ሥራዬ እና ለዚያ አሥደናቂ ድል ስላበቃኝ ኢትዮጵያዊ ፅኑ መሠረቴ ጠይቁኝ" በማለት እንደመለሰ ይነገራል፡፡

ምሩፅ በ1968 የሞንትሪያል ኦሎምፒክ ከአፓርታይድ የዘር መድልዎ ጋር በተገናኘ ኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎዋን በሰረዘች በ3 ዓመቱ ወደ ካናዳ ተመልሶ በኦታዋ የዓለም ሻምፒዮና በ5 እና 10 ሺህ ሜትሮች የወርቅ ሜዳሊያን ተቀዳጅቶ የሀገሩን ስም በድል አስጠርቶ የተመለሰ ጀግና ነው።  

ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ በ1972ቱ የሚዩኒክ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ወዳጣባት ጀርመንም ተመልሶ በ1977 በጀርመኗ ዱሰልዶርፍ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10 ሺህ እና 5 ሺህ ሜትሮች ድርብ በወርቅ ለሀገሩ ያስረከበ የምንጊዜም የኢትዮጵያ ጀግና ነው፡፡

ታላቁ ጀግና ከመም ውድድሮች ባሻገርም በግማሽ ማራቶን ተሳትፎ ድል ተጎናጽፏል፡፡ በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ መድረክ 7 የወርቅ ሜዳልያዎች ለኢትዮጵያ በማበርከት የማይፋቅ ታሪክ ጽፏል፡፡ ካደረጋቸው 310 ውድድሮች 270ዎቹን በአንደኝነት ያጠናቀቀ የትውልድ አርአያም ነው፡፡ በአሰልጣኝነት ህይወቱም ለቤጂንግ ኦሎምፒክ ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ለነቀነኒሳ እና ጥሩነሽ አሸናፊነት የራሱን አሻራ አኑሯል፡፡ በዚህ ሁሉ ገድሉ ግን ከስም በስተቀር ያገኘው ነገር አልነበረም፤ ለሀገር ይህን የመሰለ ታላቅ ውለታ ቢውልም የሚገባውን ክብር እንኳን ሳያገኝ፣ በሙያው ሠርቶ ራሱንም ሀገሩንም እንዳይጠቅም ዕድል ተነፍጎት መታከሚያ እንኳን በማጣት በችግር አለፈ፡፡ ጀግና ማክበር በቁም እያለ መሆን እንዳለበት የዚህ የሀገር ባለውለታ ጀግና ታሪክ ማስተማሪያ ሊሆን ይገባል፡፡

ማርሽ ቀያሪው ፀጥታና ሠላሙን፣ ድሉንና ታላቅ ስሙን፣ ጀግንነቱንና ኢትዮጵያዊ አይበገሬ ልቡን ይዞ ሳይወድ የሚወዳትን እና የተዋደቀላትን ሀገሩን ርቆ የሕክምና ወጪ እንኳን የሚሸፍንለት አጥቶ በቀና ግለሰቦች ድጋፍ ሕክምና ሲደረግለት ቆይቶ በካናዳ ሕይወቱ አለፈች፡፡ ታኅሳሥ 23 ቀን 2009 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክብር አረፈ፡፡ ዘላለማዊ ገድሎቹ ግን ከመቃብር በላይ ሆነው ይኖራሉ፡፡

የታሪክ ሠሪዎችን ገድል መጻፍ የሚወዱት የአውሮፓውያን ጋዜጠኞችም፣ "ማርሽ ቀያሪው እየተባለ የሚጠራው፣ በሰሜን ኢትዮጵያ አዲግራት የተወለደው ስመ ገናናው ባለድል ሯጩ ምሩፅ ይፍጠር፤ በቶሮንቶ፣ ኦንታሪዮ፣ ካናዳ ህይወቱ አለፈች" ብለው ዘገቡ፡፡

ሻምበል ምሩፅ ይፈጠር ታሪክ ሠርቶ፣ ሕዝቡን አኩርቶ፣ ዓለምን አስደንቆ ማንም ወደማይቀርበት ዓለም በሥጋ ቢለየንም አይበገሬው ኢትዮጵያዊ መንፈሱ ግን ከኢትዮጵያውያን ጋር ይኖራል፡፡ የሱን ፈለግ ተከትለው የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረጉ እንደነሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የሱ መንፈስ ተጋሪዎች ናቸው፡፡ ጅግና ቢሞት ሥራው ዘላለማዊ ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡

ለሚ ታደሰ


Feedback
Top