በተለምዶ የፋሲል ግቢ ተብለው የሚታወቁት የጎንደር ቤተ-መንግሥት ሕንጻዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ታሪካዊ ምልክቶች ሲሆኑ፤ የጎንደርን ዘመን ታላቅነት ማሳያ ምስክር ናቸው። እነዚህ የአፄ ሠርፀ ድንግል ቤተ-መንግሥት ከነበረው ጉዛራ የተቀዱ የሚመስሉ ሕንጻዎች የኢትዮጵያ ሥልጣኔ መገለጫዎችም ናቸው።
ስለነዚህ ታሪካዊ ቤተ-መንግሥቶች ሲወሳ በብዙዎቻችን አዕምሮ ውስጥ የሚመላለሰው የአፄ ፋሲል ግንብ ነው። ነገር ግን የአፄ ፋሲል ግንብ፣ የጻድቁ ዮሐንስ ቤተ-መጻሕፍት፣ የጻድቁ ዮሐንስ ግንብ፣ የአፄ ኢያሱ ግንብ፣ የአፄ በካፋ ግንብ፣ የእቴጌ ምንትዋብ ግንብና ቁስቋም ማሪያም ቤተ-ክርስቲያን በግቢው ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
ፋሲለደስ፣ ዮሐንስ ቀዳማዊ፣ ኢያሱ ቀዳማዊ፣ ሳልሳዊ ዳዊት፣ በካፋ፣ ኢያሱ ዳግማዊ፣ እቴጌ ምንትዋብ እና ኢዮአስ መዲናቸውን ጎንደር አድርገው ለ200 ዓመታት ኢትዮጵያን የመሩ ነገሥታት ናቸው። እነዚህ ነገሥታት በግቢው ውስጥ የየራሳቸውን ሕንጻ ሠርተዋል።
ፋሲል ግቢ አንኮዬ በር፣ እርግብ በር፣ ባልደራስ በር፣ ወንበር በር፣ ኳሊ በር፣ ራስ በር፣ ፊት በር፣ ግምጃ ቤት፣ ማርያም በር፣ አዛዥ ጠቋሬ በር፣ አደናግር በር፣ እምቢልታ በር እና እልፍኝ በር የሚባሉ በሮች አሉት።
ጎንደር የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና የተመሰረተችው በአፄ ፋሲል አባት አፄ ሱስኒዮስ ቢሆንም፤ በ1628 ዓ.ም በነገሡት ፋሲሊደስ አሁን ያላትን ቅርፅ ይዛ ገናና ሆናለች። ከአክሱም እና ዛግዌ ሥርወ መንግሥታት በኋላ ቋሚ ዋና ከተማ ያልነበራትን የኢትዮጵያን መዲና በጎንደር ያደረጉት አፄ ፋሲል፤ ከተማዋን የፖለቲካ፣ የሃይማኖት እና የባህል ማዕከል አድርገዋታል።
በአፄ ፋሲለደስ የተገነባው የመጀመሪያው እና ትልቁ ግንብ የተጠናቀቀው በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ነው። ቤተ-መንግሥቱ የነገሥታቱ መናገሻ ሆኖ ያገለግል የነበረ ከመሆኑም በላይ የተሠራበት ኪናዊ ውበት ለሥነ ሕንፃ ባለሙያዎች የምርምር መነሻ የሚሆን ነው። በተጨማሪም ሲሚንቶ እና ሌሎች ዘመናዊ የግንባታ ቁሳቁስ ባልነበሩበት ዘመን ከ400 ዓመታት በላይ ውበቱ ሳይደበዝዝ የቆየ ሕንጻ እንደምን ተሠራ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ነው።
በተከታታይ የተነሱት ንጉሠ ነገሥቶች ይህን ቤተ-መንግሥት በማስፋፋት አንዳንዶቹም የራሳቸውን አሻራ በማከል ከ200 ዓመታት በላይ ተጠቅመውበታል። ነገሥታቱ በየዘመናቸው ከመኖሪያቸው በተጨማሪ ቤተ-መጻሕፍትን፣ የግብዣ አዳራሾችን (ግብር ቤቶችን)፣ አብያተ ክርስቲያናትን እና መካነ እንስሳትን ገንብተዋል።
በፋሲል ግቢ ውስጥ በድንጋይ እና በኖራ የተገነቡ ከፍተኛ የምሽግ ግድግዳዎች እና የእንቁላል ቅርጽ ማማዎች መለያዎች ናቸው። አጠቃላይ ንድፎቻቸው ላይ ሀገር በቀል ዕውቀት በሰፊው የሚታይባቸው ሲሆኑ፤ ለመቃን፣ ለጉበን እና ለሰገነቶች የተጠቀሙአቸው እንጨቶች ይህን ሁሉ ዘመን ሳይበሰብሱ መኖራቸው የዚያን ዘመን የግንባታ ጠቢባን ክህሎት የሚያጎላ ነው።
በግቢው ውስጥ ከሚገኙት ግንባታዎች ትልቁና ጎላ ብሎ የሚታየው የአፄ ፋሲለደስ ግንብ ነው። በጣም አስደናቂ በሆኑ እና ምጣኔያቸውን በጠበቁ የአራት ማዕዘን ቅርጽ እና የእንቁላል ቅርጽ ባላቸው ማማዎች የሚታወቀው ይህ ግንብ እንደ በኩርነቱ የግቢው ምልክት ሆኖ ቆይቷል።
የቀዳማዊ ኢያሱ ቤተ-መንግሥት ሌላው በዚህ ግቢ ውስጥ የሚገኝ ታላቅ የጥበብ ውጤት ነው። ይህ የቀዳማዊ ኢያሱ ቤተ መንግሥት ከወርቅ ልብጥ እና ከከበሩ ድንጋዮች የተሠራ እና በጣም የተዋበ ቤተ-መንግሥት ነው። ለነገሥታቱ እና ለመኳንንቱ መሰብሰቢያ የሚያገለግሉት የግብር እና የመሰብሰቢያ አዳራሾችም በፋሲል ግቢ ውስጥ ከሚገኙ ስብሰቦች መካከል ናቸው። የእቴጌ ምንትዋብ የፈረስ ግምብም ሌላው የግቢው ውበት ነው።
ጎንደር የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ባገለገለችባቸው ወቅቶች የሥነ ጥበብ፣ የሙዚቃ እና የሥነ ጽሑፍ ማዕከልም ነበረች። ከመላው ኢትዮጵያ የተሰባሰቡ ወታደሮች፣ አገልጋዮች እና መኳንንት የከተሙባት፣ በኅብረ ቀለም የደመቀችም ነበረች። ጎንደር ከ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ የቆየው የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት መረጋጋት እና የኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ማሳያ ምልክት ናት።
የጎንደር ዘመን መዳካም የጀመረው በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ነው። ራስ ሚካኤል ስሁል በ1761 ዓ.ም ቀዳማዊ አፄ ኢዮአስን ከገደሉ በኋላ አቅማቸው ስለጠነከረ የፈለጉትን እያነገሡ፣ ያልፈለጉትን እያወረዱ ቆዩ። ይህ ድርጊታቸው በየጊዜው እያኮረፉ ወደ ሽፍታነት የሚወጡ ሰዎች እየጨመሩ እንዲሄዱ አድርጎ በመጨረሻም ዘመነ መሳፍንት እንዲመጣ ምክንያት ሆነ። ከዘመነ መሳፍንት ማብቃት በኋላ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ጎንደር መናገሻ የነበረች ቢሆንም፤ የነበራትን ድምቀት እና ተፅዕኖ ግን አጥታ ነበር። አፄ ዮሐንስ ሲነሱም ቤተ-መንግሥታቸውን በመቀሌ አድርገው የነበረ ሲሆን፤ እርሳቸው ሲያልፉ የኢትዮጵያ መዲና ወደ መሀል ሀገር መጣ።
በአምስቱ ዓመት ወረራ ወቅት ጣሊያን ሕንጻዎቹን ለወታደራዊ አገልግሎት ሲጠቀም የነበረ ሲሆን፣ በጦርነቱም ጉዳት ደርሶባቸዋል። በዚሁ ወቅት ጣሊያን ሲሚንቶ እና ኖራ በመቀላቀል እንዲሁም ከቀድሞው የተለዩ ድንጋዮችን በመጠቀም ሕንጻዎቹን ያደሰ ሲሆን፤ ይህም በነባሩ ኪነ ሕንጻ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩ ይነገራል። ለሕንጻዎቹ አሁን እየተደረገ ባለው እድሳት ይህን የማስተካከል ስራ ጭምር መከናወኑን አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ይገልጻሉ።
ፋሲል ግቢ በ1972 ዓ.ም የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ተብሎ ተመዝግቧል። በአሁኑ ጊዜ የጎንደር ቤተ-መንግሥት ዋነኛ የቱሪስት መስህብ ሲሆን፤ ከመላው ኢትዮጵያ እና ከዓለም ዙሪያ የመጡ ጎብኚዎች ይደመሙበታል። ይህ ቤተ-መንግሥት የኢትዮጵያ የኃያልነት ዘመን ማሳያ ቋሚ ምስክር እና በአፍሪካ እና በዓለም ቅርሶች ታሪክም ልዩ ቦታ ያለው ነው።
የአሁኑን የፋሲል ግቢን ዋና መቀመጫቸው ያደረጉት የአፄ ፋሲል አባት አፄ ሱስኒዮስ ቀዳማዊ ናቸው። አፄ ሱስኒዮስ ሥልጣናቸውን ወደ ልጃቸው ፋሲለደስ ያዘዋወሩበት ሂደት በታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ አለው። በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የጀመሩት ፖርቱጋላውያን በአፄ ሱስኒዮስ ዘመነ መንግሥትም ግንኙነታቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። ከንጉሡ ጋር በነበራቸው ጥብቅ ግንኙነትም ንጉሡን ሰብከው በማሳመን ሃይማኖታቸውን ወደ ካቶሊክ እንዲቀይሩ አደረጉ። ንጉሡም ራሳቸው ካቶሊክ ከሆኑ በኋላ ሕዝቡም ካቶሊክን እንዲቀበል በአዋጅ አሳወቁ። በዚያ ምክንያትም በርካታ ሰዎች ሃይማኖታችንን አንቀይርም በማለታቸው እንዲገደሉ ተደረገ፤ እርሳቸው ለሌሎች ማስፈራሪያ ይሆናሉ በማለት የፈፀሟቸው የሞት ቅጣቶች አለመረጋጋቱን አባባሰው። በዚህም ምክንያት ንጉሡ አፄ ሱስኒዮስ ሥልጣናቸውን ለልጃቸው ፋሲለደስ አስረከቡ።
አፄ ፋሲልም ሥልጣኑን እንደተረከቡ የኦርቶዶክስ ሃማኖትን በመመለስ ሚሲዮናውያኑን ከሀገር አባረሩ። በዘመነ መንግሥታቸው ከውጭው ዓለም በተለይም ከአውሮፓውያን ጋር የነበራቸው ግንኙነት እጅግ ጥነቃቄ የተሞላበት ነበር። ፈረንጆቹ የእርሳቸውን ዘመን ሲገልጹ ‘Closed Door Policy’ ይሉታል። ከአባታቸው ጋር የነበረው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እና በውጭ ግንኙነት ላይ የወሰዱት ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ ዘመነ መንግሥታቸው የተረጋጋ እንዲሆን አስተዋጽኦ ማድረጉም ይገለጻል።
ይህ የኢትዮጵያም የዓለምም ሀብት የሆነው የጎንደር ቤተ-መንግሥት በጣሊያን ወረራ ወቅት እና በተለያዩ ዘመናት በደረሰበት ጥንቃቄ የጎደለው አያያዝ ጎስቁሎ እና ፈራርሶ ሲታይ የሚያስቆጭ ነበር። አሁን ለጎንደር አዲስ ቀን ወጥቶላታል፤ ቤተ-መንግሥቷ ታሪኩን በሚመጥን መልኩ ታድሷል። የፋሲለደስ እድሳት እጅግ በጣም ውብ በሆነ፣ የከተማዋን ታሪካዊነት ይበልጥ በሚያጎላ እና የቱሪስት መዳረሻነቷን በሚያሳድግ መልኩ ተሠርቷል። የጎንደር ትንሣኤ እና መታደስ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ነው። የጎንደርን ውበት የመለሱ እጆች ነገ ኢትዮጵያን የሚገነቡ ስለሆነ፤ የጎንደር መታደስ ለኢትዮጵያ ትንሣኤ መዳረሻ ነው።
በለሚ ታደሰ