የእስራኤልና ሀማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ከጫፍ ደርሷል - ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

منذ 5 أيام
የእስራኤልና ሀማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ከጫፍ ደርሷል - ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የእስራኤልና ሀማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ፍሬ ለማፍራት ከጫፍ ደርሷል ሲሉ ተናገሩ።

ጆ ባይደን ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ከኳታሩ ኢምር ሼኽ ታሚም ቢን ሐማድ አል-ታሕኒ ጋር መምከራቸው ተገልጿል።

በኳታር አደራዳሪነት በሚደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የእስራኤልና ሀማስ ባለስልጣናት ቅድመ ሁኔታዎች ላይ መስማማታቸውም ነው የተገለጸው።

በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግና ታጋቾችን ለመለዋወጥ ሁለቱም ወገኖች ፍላጎት እንዳላቸውም ተነግሯል።

የእስራኤል ታጋች ቤተሰቦች ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሀማስ ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ ቤተሰቦቻቸውን እንዲያስለቅቁ ግፊት እያደረጉ ይገኛል ነው የተባለው፡፡

የድርድሩ ዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳይ ጊዜ ቢወስድም ሀማስና የእስራኤል ባለሥልጣኖች ተገናኝተው እየተነጋገሩ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በድርድሩ ይዘት መሰረት ሀማስ አግቶ የቆያቸውን ሰዎች በስምምነቱ የመጀመሪያ ዕለትና በተለያዩ ቀናት እንደሚለቅ ተጠቁሟል።

እስራኤል በበኩሏ ሕዝብ ከሚኖርባቸው አካባቢዎች ወታደሮቿን እንደምታስወጣና በደቡባዊ ጋዛ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ሰሜናዊው አካባቢ እንዲመለሱ እንደምትፈቅድ ተነግሯል፡፡

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሌሎች ዝርዝር ጉዳች ማካተቱ የተገለፀ ሲሆን፤ የተኩስ አቁም ከተተገበረ ከ16 ቀናት በኋላም የስምምነቱ ሁለተኛና ሦስተኛ ክፍሎች ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡

ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው የጋዛ ጦርነት እስካሁን ከ46,000 በላይ አብዛኞቹ ሰላማዊ የሆኑ ሰዎች በእስራኤል ዘመቻ ጋዛ ውስጥ መገደላቸው ተገልጿል።


ردود الفعل
Top