ባለፉት ዓመታት ለነዳጅ ድጎማ ብቻ ከ267 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል - የገንዘብ ሚኒስቴር

منذ 5 أيام
ባለፉት ዓመታት ለነዳጅ ድጎማ ብቻ ከ267 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል - የገንዘብ ሚኒስቴር

ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ከገባች በኋላ ትግበራውን ማሳካት የሚያስችሉ የተለያዩ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ተናግረዋል።

አሁን ላይ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የእድገት እንቅስቃሴ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የተለያዩ የኢኮኖሚ  አመላካቾችም ይህንን በሚገባ እንደሚያሳዩ ነው በሰጡት መግለጫ ያመለከቱት።

ከተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ ወዲህ የገቢ አሰባሰብ ማደጉ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በከፍተኛ ደረጃ መሻሻሉ፣ የወጪ ንግድ የተሻለ አፈፃፀም የታየበት መሆኑ፣ የባንኮች ቁጠባ እያደገና ለኢኮኖሚው የሚያቀርቡት ብድርም በጠንካራ ሁኔታ ላይ መገኘቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ ለአብነት ጠቅሰዋል።

ማሻሻያውን ከግብ ለማድረስም ከልማት አጋሮች ጋር ያለው ትብብር ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።

የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ የሚመራበት አሰራር ተግባራዊነትን ተከትሎም እንደ ነዳጅና ማዳበሪያ ያሉ ስትራቴጂክ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንዳይኖር መንግስት ድጎማ በማድረግ ለህዝቡ እያቀረበ መሆኑንም ተናግረዋል።

የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያን ተከትሎ ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ሊኖር የሚችል የዋጋ ጭማሪን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል ብለዋል አቶ አህመድ ሺዴ።

ለአብነትም መንግስት በአመት 4.5 ቢሊዮን ዶላር በማውጣት ነዳጅን ከውጪ ሀገር እያስገባ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ አሁን ባለው የዓለም ዋጋ በኢትዮጵያ ይሸጥ ቢባል በህብረተሰቡ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማቃለል በድጎማ እየቀረበ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ባለፉት ዓመታት በአጠቃላይ መንግስት ለነዳጅ ያደረገው ድጎማ እስከ 267 ቢሊዮን ብር መድረሱንም የገንዘብ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም በነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ አሰራር ለነዳጅ ድጎማ ይደረግ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ ሪፎርሙን ተከትሎ በተጨማሪ በጀት የገንዘብ ሚኒስቴር በቀጥታ ለነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በየወሩ እያስተላለፈ መሆኑንም አስረድተዋል።

ዘንድሮ ለነዳጅ ብቻ 100 ቢሊዮን ብር በተጨማሪ በጀት በፓርላማ ማሳወጅ የተቻለውም ህብረተሰቡ ላይ የሚፈጠር ጫናን ለማቃለል መሆኑንም ተናግረዋል።

መንግስት ለነዳጅ ድጎማ እያደረገ በመሆኑም ከዓለም እና ከጎረቤት ሀገራትም ባነሰ ዋጋ እየቀረበ ይገኛልም ነው ያሉት።

ይህን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገባ ነዳጅ በከፍተኛ ጥንቃቄ ማቅረብ እና በቁጠባ መጠቀም ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህ ረገድ ያለውን ህገወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ ለመከላከል ግብረ-ኃይል ተቋቁሟል ብለዋል።

የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎበት ወደ ትግበራ መግባቱን የጠቀሱት ሚኒስትሩ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ተጎጂ እንዳይሆኑ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለዚህም 400 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት በማሳወጅ ነዳጅን ጨምሮ ማዳበሪያ፣ መድሀኒት፣ ዘይት እና ስኳር ከውጪ ሀገር ተገዝተው ለህብረተሰቡ በድጎማ እየቀረቡ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ከዚህ ውስጥ 82 ቢሊዮን ብር ለአፈር ማዳበሪያ ግዢ ድጎማ፤ 60 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለከተማና ገጠር ሴፍቲኔት ድጋፍ ይውላል ብለዋል።

ዝቅተኛ ደሞዝ ተከፋይ ለሆኑ ሰራተኞችም ማሻሻያ መደረጉንም አንስተዋል።

ሌሎች ሀገራት መሰል ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሲተገብሩ ይህን አይነት ድጋፍ ሲያደርጉ አይታይም ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በህብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳይደርስ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ከፍተኛ ሀላፊነት የሚሰማው መንግስት መሆኑን የሚያመለክት ነው ብለዋል።

ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ስኬት ዘላቂነትም መንግስት በየጊዜው ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ በብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ በኩል የሚያከናውናቸውን የክትትልና ድጋፍ ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።

ጌታቸው ባልቻ


ردود الفعل
Top