እግር ኳስን ከባዶ እግሩ ከመጫወት እስከ አውሮፓ ክለቦች የተጓዘው ሴኔጋላዊው “ኔይማር”

منذ 6 أيام
እግር ኳስን ከባዶ እግሩ ከመጫወት እስከ አውሮፓ ክለቦች የተጓዘው ሴኔጋላዊው “ኔይማር”

የእግር ኳስ ክህሎቱን የተመለከቱ ሴኔጋላዊው ”ኔይማር” ብለው ይጠሩታል፡፡ከህፃንነቱ እስከ 16 ዓመቱ ድረስ ኳስን በጫማ ሳይሆን በባዶ እግር ተጫውቷል፡፡ ፍጥነቱ እንደ አቦ ሸመኔ በመሆኑና በሚመታቸው ጠንካራ ኳሶች በርካቶች ከዲዲየር ድርጎባ ጋርም ያመሳስሉታል፡፡ የ23 ዓመቱ ተስፈኛ ሴኔጋላዊ የቼልሲ የፊት መስመር ተጫዋች ኒኮላስ ጃክሰን፡፡

በአውሮፓ ሊጎች ድንቅ የእግር ኳስ ችሎታ ካላቸው ወጣት አፍሪካውያን ተጫዋቾች መካከል ተጠቃሽ የሆነው ኒኮላስ ጃክሰን የተወለደው በአፍሪካዊቷ ጋምቢያ መዲና ባንጁል ውስጥ ነው፡፡ እናቱ ሴኔጋላዊት ስትሆን አባቱ ደግሞ ጋምቢያዊ ነው፡፡ለእግር ኳስ ያለው ጥልቅ ፍላጎት ትምህርቱን አቋርጦ ቤተሰቡን ጥሎ ወደ ስፔን እንዲሰደድ አድርጎታል፡፡

የሴኔጋል የኳሳ ስፖርት አካዳሚን ከመቀላቀሉ በፊት በደቡባዊ ሴኔጋል ለኤ.ኤስ.ሲ እግር ኳስ ቡድን ተጫውቷል፡፡ በክለቡ ተቀይሮ በመግባት በ15 ደቂቃዎች ባሰየው ድንቅ ብቃት ሰኔጋላዊው “ኔይማር” የሚል ቅፅል ስምም ተሰጥቶታል፡፡ የእግር ኳስ ተምሳሌቱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ መሆኑን የሚናገረው ኒኮላስ ጃክሰን ወደ ፊት ብዙ ታሪክ የመስራት ህልም እንዳለው ይናገራል፡፡

በሴኔጋል በእግር ኳስ ባለተስጥኦ ወጣቶችን በመሰብሰብ ለሀገሪቱ ብቁ ተጫዋቾችን በማፍራት የሚታወቀው አካዳሚ ቆይታ በኋላ እ.አ.አ በ2017 ወደ ስፔኑ ቪያሪያል አቅንቷል፡፡


እ.አ.አ ከ2018 ጀምሮ ደግሞ ለሴኔጋል ብሄራዊ ቡድን እየተጫወት ይገኛል፡፡

ተጫዋቹ በአብሮ አደጎች ዘንድ ቁርጠኝነት ያለው፣ በሁለቱም እግሮቹ ኳስ በደንብ መጫወት የሚችል፣ ፈጣን እንዲሁም በጭንቅላቱ ግቦችን ማስቆጠር የሚችል ትልቅ ተጫዋች መሆን እንደሚችል በርካቶች እምነት ነበራቸው፡፡

በስፔኑ ቪያሪያል በነበረው ቆይታ ከአሁኑ የአስቶን ቪላ አሰልጣኝ ኦናይ ኤምሪ ጋር አብሮ የመስራት እድል በማግኘቱ የእግር ኳስ ችሎታውንና አቅሙን ማሳደግና ውጤታማ መሆን የሚችልበትን ስልጠና አግኝቷል፡፡
 
ራሱን ለማሻሻል ሁሌም የመማር ፍላጎቱ ከፍተኛ ስለሆነ ስልጠናው የተሟላ ተጫዋች እንዲሆን አግዞታል፡፡ በዚህም ለእንግሊዙ አንጋፋ ክለብ ቼልሲ ለ8 ዓመታት በመፈረም በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ ቼልሲን ከተቀላቀለበት ከ2023 ጀምሮ ወጥ አቋም ማሳየት ባይችልም ግቦችን በማስቆጠር ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ባለተስጥኦ ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል፡፡ እ.አ.አ በ2023/24 የውድድር ዓመት በ35 ጨዋታዎች 14 ግቦችን በማስቆጠር በአንድ የውድድር ዓመት ከፍተኛ ግቦችን በማስቆጠር ከመሀመድ ሳለህ ቀጥሎ 2ኛው አፍሪካዊ ተጫዋች መሆን ችሏል፡፡



እግር ኳስን በባዶ እግር መጫወት የጀመረው ኒኮላስ ጃክሰን ወደ ፈት ከቼልሲም ሆነ ከሀገሩ ሴኔጋል ጋር ብዙ ስኬቶችን ማጣጣም እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡

“በራሴ ላይ እምነት አለኝ ፤ ጠንክሬ እሰራለሁ ፤ በአፍሪካ እግር ኳስን በመንገድ ላይ መጫወት ባህል ነው ፤ እኔም ከዚህ የተገኘሁ ነኝ ፤ የቤተሰቦቼ ፍላጎት ጎበዝ ተማሪ እንድሆን ቢሆንም እኔ ግን ዘወትር በየመንገዱ እግር ኳስ የመጫወት ፍላጎቴ ከፍተኛ በመሆኑ አሁን ለደረሰስኩበት ደረጃ መሰረት ጥሏል” ይላል፡፡

በትውልድ ሀገሩ በጋምቢያ እንዲሁም ባደገበት ሴኔጋል ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች የተለያዩ ምግብና የመማሪያ ቁሳቀሶችን ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ እግር ኳስን አብረውት የጀመሩና በአውሮፓ በተለያዩ ክለቦች የሚጫወቱ ታጫዋቾችን በማስተባበር ታኬታና መሰል ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ በአፍሪካ ተስጥኦ ላላቻው ታዳጊዎች ድጋፍ ያደርጋል፡፡


በአሰልጣኞች ዘንድ ቴክኒክና በታክቲክ በስልጠና ማደግ የሚችል አቅም ያለው ዳይመንድ ፤ በእንግሊዝ ምርጥ አጥቂዎች መካከል አንዱ መሆን እንደሚችል የተነገረለት ኒኮላስ ጃክሰን የወደፊት ህልሙን ለማሳካት እየተጋ ይገኛል፡፡


በላሉ ኢታላ


ردود الفعل
Top