የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እና የሰላማዊ ፖለቲካ አቀንቃኙ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

منذ 14 أيام
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እና የሰላማዊ ፖለቲካ አቀንቃኙ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

“ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ሌላ፤ ኦሮሞነት ደግሞ ሌላ ነው፤ ኦሮሞነቴ ከኢትዮጵያዊነቴ ጋር ተጋጭተውብኝ አያውቁም” በማለት ይታወቃሉ። የካበተ ልምዳቸውን ለሀገራቸው ለማዋጣት አልሰሰቱም። “ኢትዮጵያ ከፍ የምትለው ተባብረን ስንሠራ ነው” ሲሉም ብዙ ጊዜ ይደመጣሉ። ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጭ የፖለቲካ አካሄድ ከውድመት ውጭ ለውጥ እንደማያመጣ ከመናገርም አልፈው በሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ ተወዳድረው ፓርላማ በመግባት ለሕዝባቸው ድምፅ ለመሆን በቅተዋል።

በዛሬው ዕለት በ94 ዓመታቸው ያረፉት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ስፍራ አላቸው። በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር እንዲሁም የዓለም ባንክ የአፍሪካ ተወካይ በመሆን ሠርተዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቀጥረው በተለያዩ ሀገራት አገልግለዋል።

አቶ ቡልቻ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቦጂ ቢርመጂ ወረዳ ከአባታቸው አቶ ደመቅሳ ሰንበቶ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ናሲሴ ሰርዳ በ1923 ዓ.ም ተወለዱ። አባታቸውን በልጅነት በሞት ቢያጡም አጎታቸው ጎቡ ሰንበቶ አሳድገዋቸው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ አድርገውላቸዋል። የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጊምቢ አድቬንቲስት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኩየራ አድቬንቲስት ተምረዋል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ እና በሕግ ዲግሪዎች ተመርቀዋል። በወቅቱም በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ከተመረቁ 10 ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆን ወደ አሜሪካ በመሄድ በሲራኪዩዝ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ወደ ኢትዮጵያ በመመለስም በኢኮኖሚው መስክ የራሳቸውን አሻራ አኑረዋል። አቶ ቡልቻ በዘመናዊ የግል ንግድ ባንኮች ምሥረታ ታሪክ ተጠቃሽ የሆነው የአዋሽ ባንክ መሥራች ናቸው።

በምጣኔ ሀብቱ ያካበቱትን ልምድ በመያዝም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተቀላቅለዋል። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራቲክ ንቅናቄን በመመሥረት እና ሊቀመንበር በመሆን በፖለቲካው ላይ የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል።ፓርቲያቸውን ወክለው በፓርላማ አባልነት ለአምስት ዓመታት አገልግለዋል።

አቶ ቡልቻ ኢትዮጵያን ሲገልጹ፣ “ባህሏ እና ታሪኳ ራሱን የቻለ ልዩ ስለሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰቱ ነገሮች ከሌላው ዓለም ጋር ለንጽጽር መቅረብ የለባቸውም” ይላሉ። ይህን ጉዳይ አስመልክተው በአንድ ወቅት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ “ኢትዮጵያ እንደ ሌላው የአፍሪካ ሀገር ዓይነት አይደለችም፤ የፈረንጅ ሀገርም አይደለችም፤ ባህሏም ኑሮዋ እና ታሪኳም የሌላ ሀገር አይደለም። ራሷን የቻለች ብቸኛ ሀገር ነች፤ በሌላ ሀገር የሆነ ሁሉ በሀገሪቱ ይሆናል ማለት አይቻልም፤ ስለዚህ ኢትዮጵያ ልዩ ሀገር ነች” ሲሉ ገልጸዋት ነበር።

አቶ ቡልቻ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሆነው ከቆዩ በኋላ ወደ አሜሪካ ሀገር ሄዱ። ደርግ ሥልጣን ሲይዝ ውጭ ስለነበሩ ወደ ሀገር ቤት ሳይመለሱ በዚያው ቆዩ። በኋላም ኢትዮጵያን እና ሌሎች 18 የአፍሪካ ሀገራትን ወክለው በዓለም ባንክ ውስጥ ሠርተዋል፡፡ በባንኩ ኢትዮጵያን በመወከል የቦርድ አባል፣ እንዲሁም የመጀመሪያው የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ተወካይ ሆነው ሠርተዋል። በዚህ ውክልናቸውም ባንኩ የሚያበድረውን ገንዘብ ከፍ ለማድረግ፣ ገንዘቡ ለታለመለት ሥራ መዋሉ እና ሥራው መካሄዱን መከታተል፣ ብድር የተሰጠው ፕሮጀክት በተባለው ጊዜ እንደሚያልቅ ለማረጋገጥ ክትትል ያደርጉም ነበር። እርሳቸው በባንኩ በነበሩበት ጊዜ “አውራ ጎዳና” ይባል በነበረው ፕሮጀክት አማካኝነት ብዙ መንገዶች በኢትዮጵያ የተገነቡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የጠየቀችው የብድር ጥያቄ እንዳይቀነስ ይታገሉም ነበር።

ኢትዮጵያ ሰላም ስታገኝ ሁሉም ነገር እንደሚሻሻል የሚናገሩት አቶ ቡልቻ፣ ያሉትን ግጭቶች እና ጦርነቶችን ለማስቆም አዋቂዎች መሪዎቻቸውን በማነጋገር እንዲስማሙ እና እንዲታረቁ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ይመክራሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሊደረግ የሚገባው ትግል ሰላማዊ እና አንድነቷን የሚያጠናክር መሆን እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ። ወደ ፖለቲካ ሲመጡ የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን (ኦነግ)ን ያልተቀላቀሉት በዚሁ አመለካከታቸው ከወቅቱ አመራሮች ጋር ስላልተስማሙ እንደሆነ ተናግረው ነበር። ሁኔታውን ሲገልጹም፣ “ኦሮሞ ከኢትዮጵያ ተለይቶ መኖር አይችልም አልኩአቸው፤ እነርሱ ጋር ያልገባሁትም ‘ኦሮሞ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ሌላ ሀገር ይሆናል’ የሚለውን ሐሳባቸውን ተቃውሜ ነው” ብለዋል። የኦሮሞ ሕዝብ የታገለው ጭቆናን ለማስቀረት ነው የሚሉት አቶ ቡልቻ፣ “ኦሮሞ ለብቻው ተገንጥሎ በየት በኩል የውጪ ንግድ ሊሠራ ይችላል? ባህሉን እንዴት ሊያስተዋውቅ ነው ወይስ ዘግቶ ሊቀመጥ? ለሁሉም የሚበቃ ሀብት ስላለን ከሌሎች ጋር በአንድነት አልምቶ መጠቀም ይሻላል” ይላሉ።

አቶ ቡልቻ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የፀና አቋም እንዳላቸው በተለየዩ ወቅቶች ባደረጓቸው ንግግሮቻቸው አሳይተዋል። ይህንኑ አቋም ሲገልጹም፣ “ኢትዮጵያ እንዳለች፣ እንደ ነበረች፣ አንድ ሆና እንድትቆይ እፈልጋለሁ፤ ሁሉንም የሚጠቅመው ይኸ ነው” ይላሉ። የግል ማንነት ከሀገር ማንነት ጋር ፈጽሞ መጋጨት እንደሌለበት አቶ ቡልቻ ይናገራሉ። ሁለቱንም አስማምቶ ለሀገር ዕድገት መሥራት እንደሚቻል እንዲህ በማለት የራሳቸውን ልምድ ያካፍላሉ፣ “ኦሮሞነቴ እና ኢትዮጵያዊነቴ ተጋጭተውብኝ አያውቁም፤ ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ሌላ፣ ኦሮሞነት ደግሞ ሌላ ነው። ኢትዮጵያዊነት ለሌላ ነገር ነው የሚያገለግለው። ውጭ ሀገር ስሄድ ‘ምንድን ነህ?’ ተብዬ ስጠየቅ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብዬ እመልሳለሁ። ኦሮሞ ነኝ ብል አይገባቸውም፤ ይህ ደግሞ ለእኔ በጣም አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያዊነት ለእኔ በጣም ከፍተኛ ነው” በማለት።

"ካለፈው ታሪክ መልካሙን በመውሰድ የሚታረሙትን በማረም ለቀጣይ ዕጣ ፈንታችን መሥራት እንጂ በታሪክ መጣላት የለብንም" ይላሉ። "ከዛሬ መቶ ዓመታት በፊት የነበሩ ሰዎች ስህተት ሠርተዋል ብለን እነሱን መውቀስ ውስጥ ከገባን እንሳሳታለን፤ እነሱ ያኔ ያስተዳደሩበት፣ የቀጡበት፣ ያስገበሩበት ስልት ዘመኑ የሚጠይቀው እና አሁን ሠለጠኑ የምንላቸው እነ አውሮፓ ይጠቀሙበት የነበረውን ስልት እንደሆነ በመጥቀስ ወደኋላ ተመልሰን እንደነዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ የምንወዛገብ ከሆነ ከእውነታ ጋር እንጣላለን" በማለት ያስረዳሉ።

አቶ ቡልቻ ስለ ምጣኔ ሀብት ዕድገት መመዘኛ ሲናገሩ፣ ለውጡ በሰዎች ተጠቃሚነት ላይ መታየት እንዳለበት ይገልጻሉ። ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ሳይጨናነቁ ማሟላት ከቻሉ፣ ከታመሙ ታክመው መዳን ከቻሉ፣ የመሠረት ልማቶች ፍትሐዊ ተጠቃሚ ከሆኑ ያኔ ምጣኔ ሀብቱ ማደጉ በተግባር ይታያል ይላሉ።

እንደ ምሳሌም ሲያነሱ፣ “ታይዋን፣ ቻይና፣ ኮሪያ፣ ጃፓን በከፍተኛ ሁኔታ አድገዋል። ይህ ዕድገታቸውም በዜጎቻቸው ሕይወት ውስጥ ይታያል። አፍሪካ ውስጥም ናይጄሪያ እና አንጎላ ነዳጅ በማግኘታቸው አድገዋል። እነዚህ በዜጎች ሕይወት እና በአጠቃላይ በሀገር ደረጃ በሚታዩ ለውጦች ያደጉ ሀገራት ለትክክለኛ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ምሳሌ ይሆኑናሉ” በማለት ይናገራሉ።

"የኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮ እንዲሻሻል እመኛለሁ" የሚሉት አቶ ቡልቻ፣ ዋናው የሕዝቡ በሽታ ድኅነት እንደሆነ ይገልጻሉ። ለዚህ ደግሞ ግብርና እንዲስፋፋ ፈጣሪ የሰጠንን መሬት በደንብ መጠቀም ያስፈልጋል ይላሉ። “ይህ ከሆነ አርሶ አደሩ ብዙ እንስሳት ይኖሩታል፤ ተሽከርካሪ ይገዛል፤ ቴክኖሎጂ ይጠቀማል፤ ልጆቹን በአግባቡ ያሳድጋል፤ ኑሮው ይሻሻላል፤ ዘመናዊ ቤትም ይገነባል። ይህ በኢትዮጵያ እንዲሆን እመኛለሁ” ይላሉ። ይህ ሁሉ እውን እንዲሆን ግን መንግሥትም ሰላም አግኝቶ ወደ ሥራ እንዲመለስ ሰላም ማውረድ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ መናናቅ የመበዛበት እና መከባበር የራቀው መሆኑን የሚገልጹት አቶ ቡልቻ፣ እንደዚህ ዓይነት አካሄዶች ከ60ዎቹ ጀምሮ ብዙ ዋጋ ስላስከፈለን ስክነት ያስፈልጋል በማለት ስለ ሰላማዊ የፖለቲካ አስፈላጊነት ይናገራሉ። በመናናቃችን እና በመገዳደላችን ምክንያት ብዙ ምሁራን ሸሽተው ሀገር ለቀው ተሰደው ሀገራችን የተማረ ሰው እንድታጣ አድርጓታልም ይላሉ።

"መከባበር ከሌለ፣ ሕዝብ ካልተባበረ፣ መነጋገር እና መደማመጥ ካልቻልን፣ ዋናው ችግራችን ድህነታችን መሆኑን አምነን እሱን ለመታገል ካልወሰንን ውኃ ላይ ቁጭ ብለን እንጠማለን፤ ሀገርም በምንም ሁኔታ አይረጋጋም በማለት ችግሮቻችንን በስክነት መፍታት አለብን" በማለት ይመክራሉ።

በሕዝቦች መካከል የሚዘራ ጥላቻ በጣም አደገኛ መሆኑን በማውሳት ተጎራብቶ፣ ተጋብቶ፣ ተዋልዶ የማይበጠስ ኅብር የፈጠረውን ሕዝብ ከማለያየት ይለቅ ችግሮች ካሉም ሕዝቡን አነጋግሮ መፍትሔ ማበጀት በእንሚያስፈልግ ይናገራሉ።

አቶ ቡልቻ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ላበረከቱት አስተዋፅኦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና አዋሽ ባንክ ሽልማት አበርክተውላቸዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርስነት የሚያዝ የልዩ ታሪካዊ ሁነቶች ማስታወሻ የወርቅ ሳንቲም የሸለማቸው ሲሆን፣ አዋሽ ባንክ ደግሞ የምስጋና የምስክር ወረቀት፣ ካባ እና የወርቅ ሜዳሊያ አበርክቶላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ያለፉትን አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ለገር የሚችሉትነ ሁሉ ማበርከታቸውን በማውሳት፣ አሳቸውን የመሰሉ ታላቅ ሰው ማጣት ለሀገር ጉዳት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በእሳቸው እረፍት የተሰማቸውን ሀዘንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንም በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለአድናቂዎቻቸው መጽናናትን ይመኛል፡፡

በለሚ ታደሰ


ردود الفعل
Top