አውሮፓውያኑ 2024ን አጠናቀው ዛሬ አዲሱን ዓመት ተቀብለዋል፤ ለመሆኑ 2024 እንዴት አለፈ?

منذ 19 أيام
አውሮፓውያኑ 2024ን አጠናቀው ዛሬ አዲሱን ዓመት ተቀብለዋል፤ ለመሆኑ 2024 እንዴት አለፈ?

የፈረንጆቹ 2024 የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎችን፣ ግጭቶችን፣ በፖለቲካው እና በተለያዩ ዘርፎች ጉልህ ዓለም አቀፍ ክስተቶችን አስተናግዶ አልፏል።

የተጠናቀቀው ዓመት ዓለም በከፍተኛ ተፈጥሮ አደጋዎች የተጠቃችበት ነበር፡፡ በዓመቱ በሬክተር መለኪያ 7.4 የደረሰ ከፍተኛ ርዕደ መሬት በታይዋን ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ ላይ በመከሰቱ በጃፓን የኦኪናዋ ግዛት አንዳንድ ክፍሎች ላይ ሱናሚ አስከትሏል። 

 

በብራዚል ሪዮ ግራንዴ ዶ ሱል ግዛት የተከሰተው ከባድ ጎርፍ በርካታ ሰዎች እንዲሞቱ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል። በተመሳሳይም በኬንያ እና በታንዛኒያ የደረሰው የጎርፍ አደጋ ከፍተኛ የሆነ የሕይወት መጥፋት እና መፈናቀል አስከትሏል።

በኢትዮጵያም  በጎፋ ዞን፣ በወላይታ ዞን እና በሰሜን ጎንደር ዞን የተከሰቱት የመሬት መንሸራተቶች በርካቶች የሞቱበት እና የተፈናቀሉበት ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡

በዓለም ላይ የጂኦፖለቲካል ለውጦች የታየበት ዓመትም ነበር፡፡ በርካታ ምርጫዎች የተካሄዱበት ዓመት ሲሆን አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ህንድ እና የአውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ ከ60 በላይ ሀገራት ምርጫ አካሂደዋል፡፡ ይህም የዓለምን ግማሽ የሚጠጋ ሕዝብ ምርጫ ሂደት ውስጥ ማለፉን አመላካች ነው። የአሜሪካው ተመራጭ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ለደጋፊዎቻቸው ንግግር እያደረጉ በተተኮሰባቸው ጥይት ጆሯቸውን የተመቱት በተጠናቀቀው ዓመት ነው። 

የሩሲያ-ዩክሬን፣ የእስራኤል-ሃማስ፣ የቻይና-ታይዋን ጦርነቶች  እና ውጥረቶች የዓለምን አሰላለፍ ይቀይራሉ ተብሎ ቢጠበቅም የተጠበቀውን ያክል ለውጥ ያልመጣበት እና ውጥረቶቹም ከመባባስ ባለፈ መፍትሄ ያላገኙበት ዓመት ነው። ይሁን እንጂ የቀድሞዎቹን ኃያላን ሀገራትን ሊገዳደሩ የሚችሉ አዳዲስ ሀገራት እና ቡድኖች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩበት ዓመትም ሆኗል፡፡

ብሪክስ ኢትዮጵያን እና ሌሎች አዳዲስ አዳጊ አባል ሀገራትን በማካተት በኢኮኖሚ እየጎለበተ መሆኑን ያሳየበት ዓመት ነው። በ2024 መጀመሪያ ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት አዳዲስ አባል ሀገራትን በመቀበል ጥምረቱን ወደ አስር ያሳደገው ብሪክስ፤ በዓመቱ ባካሄደው 16ኛ መደበኛ ጉባኤው አልጄሪያ፣ ቤላሩስ፣ ቦሊቪያ፣ ኩባ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ካዛክስታን፣ ማሌዥያ፣ ናይጄሪያ፣ ታይላንድ፣ ቱርክ፣ ኡጋንዳ፣ ኡዝቤኪስታን እና ቬትናም አዳዲስ አባል ሀገራት እንዲሆኑ ማመልከቻቸውን ተቀብሎ አጽድቋል። ይህም ጥምረቱ ወደ 23 አባል ሀገራት የሚያሳድግ ሲሆን፣ በስርጭት ደረጃም የሁሉንም አህጉራት ስብጥር እንደሚጨምር ማሳያ ነው፡፡ 

 

የተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት ተቋማት እና መንግሥታት ጄነሬቲቭ ኤ.አይ ላይ ያላቸው ግንዛቤ በእጅጉ የተቀየረበት ዓመት ነበር። የአርቴፊሻል ኢንተለጀነስ ጉዳይ የሁሉም የመገናኛ ዘዴዎች ዋና ጉዳይ ሆኖ ዓለም ላይ የአስተሳሰብ እና ተግባር ለውጥ የታየበት ሆኗል።

የጄነሬቲቭ ኤ.አይ መተግበሪያዎች በጋዜጠኝነት ዘርፍ እንኳን ብናየው ስክሪፕት ለመጻፍ፣ ወደ እውነት የተጠጋ ምስል ለመፍጠር፣ ስክሪፕት ለማንበብ ወይም ወደ ድምጽ ለመቀየር፣ ድምጽ እና ምስል ለማቀናበር እና ዜና ወይም ታሪክ ለመጻፍ አስችሏል። የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ክሶች፣ ሕጎች እና ደንቦቸ እንዲሁም የደህንነት ጥሰቶችን ስንመለከት መንግሥታት እና ተቋማት ገና ተረድተው ያልጨረሱት ጉዳይ እንደሆነ አመላካች ነው።

በተለይ ተቋማት የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጉዳይ ላይ አተኩረው የሠሩበት ዓመት ሲሆን ለዚህም ነው እንደ ሜታቨርስ፣ ስፓሻል ኮምፒውቲንግ እና ኳንተም ኮምፒውቲንግ ቴክኖሎጂዎች ላይ ጭምር በማተኮር የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት ያገኘው። ዘርፉ አዲስ እውቀት እና ክህሎት የሚፈልግ በመሆኑ ከነባሩ ዘዴ በመውጣት በዚህ አዲስ ዘርፍ ላይ ማተኮር እየተለመደ መጥቷል።

ዓመቱ በርካታ ስፖርታዊ እና የመዝናኛ ሁነቶች የተስተናገዱበትም ነበር፡፡ በመክፈቻው ላይ ባሳየው ትርኢት ብዙዎችን ያወዛገበው እና መነጋገሪያ የሆነው የፓሪስ ኦሎምፒክም የተካሄደው በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት ነው፡፡ የስፔን አሸናፊነት የተጠናቀቀው የአውሮፓ ዋንጫ እና አርጀንቲና የዋንጫ ባለቤት የሆነችበት ኮፓ አሜሪካ ዋንጫዎች የተካሄዱት በ2024 ነው። የስፔኑ ኃያል ሪያል ማድሪድ በ11 ዓመታት 6ኛ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫውን አግኝቷል፤ ማድሪድ የስፓኒሽ ላሊጋን ጨምሮ በአጠቃላይ አምስት ዋንጫዎችን በማሳካት የሚያክለው አልተገኘም፡፡

ስዊድን 32ኛ የኔቶን አባል ሀገር ሆና ቡድኑን ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት ያገኘው በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት ነው፡፡ ከሀገሯ የተሰደዱ አማጽያንን ታስጠልላለች በማለት የስዊድንን የአባልነት ጥያቄ ያልተቀበለችውን ቱርክን በማግባባት ነው ስዊድን ለረጅም ጊዜ የሕብረቱ አባልነት ጥያቄዋ ምላሽ ማግኘት የቻለችው፡፡

በዓመቱ ቻይና እና ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ቃል ገብተዋል። የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒነግ ዛሬ በጀመረው አዲስ ዓመትም ለሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን እና ለቭላድሜር ፑቲን በተናጠል መልዕክት ልከዋል። በዚህ መልዕክታቸውም ሩሲያ ጦርነቱን በድል እንድታጠናቅቅ እና ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚሹ ገልጸዋል።

ዢ በመልዕክታቸው ከፑቲን ጋር ያለንን ቅርብ ግንኙነት ለመጠበቅ እና አጠቃላይ አቅጣጫን ለማስቀጠል ቻይና ዝግጁ ናት ብለዋል። በዚህም የመጪው ዘመን ጥሩ ወዳጅነት፣ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂክ ትብብር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብር ይኖረናል ብለዋል። የቻይና -ሩሲያ ግንኙነት ሁል ጊዜ እጅ ለእጅ የመያያዝ፣ ከግጭት የጸዳ እና ገለልተኝነት ላይ ያተኮረ መሆኑን በአጽናኦት ገልጸዋል።

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ በመልዕክታቸው 2024 ትርጉም ያለው ጉዞ መሆኑን በመግለጽ፣ ሀገራቸው ከሩሲያ ጋር ያላትን እያደገ የመጣ ትብብር ታሳድጋለች ብለዋል። ኪም እና ፑቲን በተጠናቀቀው ዓመት ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ሁሉን አቀፍ የትብብር ስትራቴጂክ ስምምነት ተፈራርመዋል። በዚህ ስምምነት መሰረት በሁለቱ ሀገራት ላይ ሦስተኛ አካል ጦርነት የሚከፍት ከሆነ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ የሚያስችላቸው እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ከ2022 የካቲት ጀምሮ እስካሁን ባልበረደው የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ የወታደሮች ድጋፍ እንደምታደርግ ደቡብ ኮሪያ፣ አሜሪካ እና ኔቶ ሲወቅሱ መቆየታቸው የሚዘነጋ አይደለም። 

በጌቱ ላቀው

 

 


ردود الفعل
Top