ከአየር መንገዱ ስኬት ጀርባ ያለው ዩኒቨርስቲ

منذ 23 أيام
ከአየር መንገዱ ስኬት ጀርባ ያለው ዩኒቨርስቲ

የኢትዮጵያ አቪየሽን አካዳሚ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ 8 ስትራቴጂክ የቢዝነስ ዩኒቶች አንዱ ነው፡፡ ዩኒቨርስቲው በየዓመቱ 4 ሺህ ሠልጣኞችን የመቀበል አቅም ያላቸው አምስት ትምህርት ቤቶች አሉት።

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዕውቅና የተሰጠው የሥልጠና ተቋም ነው፡፡ የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪየሽን ድርጅት (ICAO) የቀጣናው የሥልጠና ማዕከልነትን ዕውቅና አግኝቷል፡፡

በአውሮፓ አቪዬሽን ደህንነት ኤጀንሲ (EASA) በክፍል 147 የB737 እና B757/767 የጥገና ማሠልጠኛ ተቋምነት ማረጋገጫ አለው፡፡ በዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) ማረጋገጫም ተሰጥቶታል፡፡ ሌሎች የዘርፉ ባለድርሻዎችም ለአካዳሚው የማረጋገጫ የምስክር ወረቀቶችን እና ሽልማቶችን አበርክተዋል፡፡ 

ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) የቀጣናዊ የሥልጠና አጋርም ነው የኢትዮጵያ አቪየሽን ዩኒቨርስቲ፡፡ በዓለም አቀፍ የአቪየሽን ማሰልጠኛ ተቋማት በተደረገ ምዘናም አራተኛውን ከፍተኛ ደረጃ ያገኘ ተቋም ነው፡፡

ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ እድሜ ያለው የኢትዮጵያ አቪየሽን አካዳሚ በቀጣናው ትልቁ እና ዘመናዊ የበረራ እና ቴክኒክ ማሰልጠኛ ማዕከል ሲሆን፣ ምርጥ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የታጠቀ ነው።

የምስለ በረራ (simulator) ቴክኖሎጂ ፕሮግራምን በማስተዋወቅ እና በተሳካ ሁኔታ በማካሄድ ላይ ከሚገኙ ጥቂት የአፍሪካ የአቪየሺን የሥልጠና ማዕከላትም የመጀመሪያው ነው።

በአፍሪካ ደረጃ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለው እና ትልቁ የአቪየሽን ሥልጠና አካዳሚ ተግባራዊ እና የሥራ ላይ ሥልጠናዎችን ለመስጠት የሚያስችሉ ዘመናዊ አውሮፕላኖች፣ የማሠልጠኛ መሣሪያዎች እና የጥገና ተቋማት ባለቤት ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሥልጠና መስፈርት ያሟላው የኢትዮጵያ አቪየሽን አካዳሚ ሠልጣኞቹን በከፍተኛ ደረጀ የሚያበቁ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የታጠቀ ነው፡፡ በዚህም በዓለም አቀፍ እና በአፍሪካ ደረጃ ከፊት ከሚሰለፉት ብቁ ተቋማት አንዱ በመሆኑ የብዙዎች ምርጫ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አቪየሽን አካዳሚ የተቋቋመው በ1957 ዓ.ም ነው፡፡ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ ከ52 በላይ ሀገራት የመጡ 16 ሺህ ገደማ የአውሮፕላን ባለሙያዎችን አሠልጥኖ አብቅቷል።

በ1964 ዓ.ም የአብራሪዎች ማሠልጠኛ፣ በ1967 የአውሮፕላን ጥገና ቴክኒሽያን፣ በ1981 ደግሞ የማርኬቲንግ እና የፋይናንስ ትምርት ቤቶች ሥራ እንደጀመሩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የፓይለቶች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ ባለፉት 58 ዓመታት ውስጥ በመላው አፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በእስያ እና በአውሮፓ ከሚገኙ 52 ሀገራት የተውጣጡ አብራሪዎችን በብቃት አሰልጥኖ ወደ ሥራ አሰማርቷል።

የፓይለት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ በአሁኑ ወቅት ባለብዙ ሞተር ደረጃ መሣሪያዎች (CPL/IR/ ME) እና በምስለ በረራ ለንግድ የፓይለትነት ፈቃድ እውቅና ያላቸው የሥልጠና ፕሮግራሞች አሉት። በተጨማሪም ለአብራሪ አሰልጣኞች፣ ለበረራ ስምሪት ባለሙያዎች እና ምስለ በረራ አሠልጣኞች ሥልጠናዎችን ይሰጣል።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ 8 ስትራቴጂክ የቢዝነስ ዩኒቶች ውስጥ የኢትዮጵያ አቪየሽን አካዳሚ አንዱ ሲሆን፤ የዓለም አቀፍ ደንበኞች አገልግሎት፣ የሆቴልና ቱሪዝም አስተዳደር፣ የሀገር ውስጥና ቀጣናዊ አገልግሎት፣ የካርጎ እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ የጥገና እና ቴክኒክ አገልግሎት፣ የበረራ ላይ መስተንግዶ አገልግሎት፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ቁጥጥር አገልግሎት የአየር መንገዱ ሌሎቹ የቢዝነስ ዩኒቶች ናቸው፡፡  

አካዳሚው ቀድሞ የነበረውን ሰዓት ላይ የተመሠረተ የሥልጠና ሥርዓት በመቀየር በብቃት ላይ የተመሠረተ ሁለገብ ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡ ሠልጣኞች በተለያዩ የአውሮፕላኖች ላይ ሥልጠና የሚወስዱ ሲሆን፣ ሲሙሌተር እና ትክክለኛ አውሮፕላንን በመጠቀም ሁለገብ ብቃት የሚያጎናጽፋቸውን ክህሎት እንዲያገኙ ይደረጋሉ፡፡

እየጨመረ የመጣውን በበረራ ወቅት የሚያጋጥሙ ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ አደጋዎችን ለመከላከል የበረራ ከቁጥጥር ውጭ መሆንን መከላከል እና ሲከሰትም በአግባቡ የማስተዳደር (UPRT) ሥልጠናም ይሰጣል፡፡

የአውሮፕላን ጥገና ትምህርት ቤቱ በዲፕሎማ ደረጃ እና አጫጭር የተግባር ሥልጠናዎችን ይሰጣል። ይህ ሥልጠና የዘመናዊ የአውሮፕላን ጥገና ሥልጠናዎችን ሙሉ ለሙሉ የሚሸፍን ነው። በየጊዜው የሚለዋወጠውን የአቪየሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የንድፈ-ሐሳብ እና ተግባራዊ ሥልጠናውን ሚዛናዊ በማድረግ ብቁ ባለሙያዎችን በማፍራትም ይታወቃል፡፡

የስምሪት ባለሙያዎች ሥልጠና የበረራ ዝግጅትን ቁጥጥር እና ክትትል፣ የበረራ መረጃ አያያዝ፣ የኦፕሬሽንና የአየር ትራፊክ አገልግሎት (ATS) የበረራ እቅድ ዝግጅት እና የበረራ ላይ ግንኙነትን ያካተተ ነው፡፡

የካቢን ሠራተኞች ማሰልጠኛ ማዕከል ለዓመታት ጥራቱን የጠበቀ ሙያዊ ሥልጠና እየሰጠ ያለ ግንባር ቀደም ትምህርት ቤት ነው፡፡ ይህ የማሠልጠኛ ማዕከል ከ58 ለሚበልጡ ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ጥራቱን የጠበቀ እና ሥነ-ምግባር ላይ የተመሰረተ ሥልጠናን በመስጠት በኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ዝና አትርፏል።

የኮሜርሺያል እና ግራውንድ ኦፕሬሽንስ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በአውሮፕላን ማረፊያ እና በካርጎ ሥራ ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉት ሀሉ ሥልጠና ይሰጣል። የሥልጠናው ዋና ዓላማ ሠራተኞች አጠቃላይ ደንቦችን እንዲያውቁ የሚያስችል ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ አቪየሽን ባለ ሥልጣን እና ከዓለም አቀፍ የአቪየሽን ባለሥልጣናት ደረጃዎች ጋር የሚናበቡ ጥልቀት ያላቸው የሥልጠና ፕሮግራሞችን ያካሄዳል። ሠልጣኞቹ ሁሉንም ተያያዥ ፖሊሲዎች፣ አሠራሮች እና የትግበራ ሂደቶችን የተመለከቱ መረጃዎችን እና መመሪያዎችን የሚያገኙት ፈቃድ ካላቸው መምህራን ሲሆን፣ ሥልጠናውን በብቃት ካጠናቀቁ የምስክር ወረቀት ያገኛሉ።

አካዳሚው የአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራሮች ይበልጥ ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሥልጠናም እየሰጠ ነው። የሰው ኃይል ልማት ፕሮግራሙ (MDP) አየር መንገዱ በአፍሪካ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ አመራር እንዲኖረው አስችሏል።

ሠልጣኞቹ ትርፍ ሰዓታቸውን የቅርጫት ኳስ በመጫወት፣ የቤት ውስጥ ስፖርቶች፣ በጂም ውስጥ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ እንዲሁም በአካዳሚው ውስጥ ባሉ ጽዱ አካባቢዎች በመንሸራሸር በደስታ ያሳልፋሉ።

60ኛ ዓመቱን እያከበረ ያለው አካዳሚው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጀርባ አጥንት ነው፡፡ ከዚያም አልፎ በርካታ የአፍሪካ እና የመካከለኛ ምሥራቅ የአቪየሺን ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ማብቃት የቻለ ነው፡፡ በቀጣይም የዘርፉን የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ሥልጠና መስጠቱን ይቀጥላል፡፡

በለሚ ታደሰ


ردود الفعل
Top