የትውልዱ ጥያቄ፤ የኢኮኖሚው የደም ቧንቧ፦ ቀይ ባህር

منذ 24 أيام
የትውልዱ ጥያቄ፤ የኢኮኖሚው የደም ቧንቧ፦ ቀይ ባህር

ከ10 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም የንግድ ሸቀጥ የሚተላለፍበት፤ 11 ሀገራት የጦር ሰፈር የመሰረቱበት፣ ዓለም አቀፍ ኃይሎች የጂኦፖለቲካ ሽኩቻ የሚያካሂዱበት ቀይ ባህር የኢትዮጵያ የትውልድ ጥያቄ ነው። 

በቀደመው ጊዜ በተሰሩ ስህተቶች ሀገራችን ያጣችው የባህር በር የለውጡ ዋንኛ ትኩረት፤ የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ መጥቷል። 

ይህ የባህር በር ጥያቄ በተለይ ከለውጡ በፊት አይነኬ ተደርጎ የቆየ ሲሆን፤ አሁን ላይ ከአስተሳሰብ ለውጥ ጀምሮ ተጠቃሚነትን እስከ ማረጋገጥ የደረሰ የቁርጠኝነት እና የተግባር ስራ እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዲ ዘነበ ይናገራሉ። 

ከታሪክ ለመረዳት እንደሚቻለው ሀገራችን ስትራቴጂክ በሆነ ሁኔታ የባህር በር እንድታጣ ከመደረጓ በተጨማሪ፤ ያንን በተመለከተ የሚቋቋሙ ፎረሞች ላይ ተሳታፊ እንዳልተደረገች እሙን ነው። ለዚህም በሳውዲ አረቢያ አስተባባሪነት የተመሰረተው እና 8 ሀገራትን ያቀፈው የቀይ ባህር ፎረም (The Red Sea Forum) ጥሩ ማሳያ ነው።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሀገራችን አተኩራ ስትሰራበት በነበረው በዚህ ጉዳይ በተለይም ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ተከትሎ ከፍተኛ ጫና ሲደረግባት እንደነበር ዶ/ር አብዲ ያስታውሳሉ። 

በሳል ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴን በመጠቀም የተከናወነው ስምምነት ቀጣናውን ለማተራመስ በሚፈልጉ አካላት ላይ ውሃ የቸለሰ ሆኗል ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ከኢቢሲ ዶትስትሪም ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል። 

የአንካራው ስምምነትም ሶማሊያ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ የተቀበለችበት እና ሕጋዊነቱን ያጠናከረችበት መሆኑን ያነሳሉ። 

የትውልድ የሆነው የባህር በር ጥያቄ ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ስትራቴጂያዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን የሚገልፁት ዶ/ር አብዲ፤ አንዲት ሀገር ከባህር ስትርቅ ውስጣዊ ያለመረጋጋቶችን ከማስተናገድ ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ፈጠራዎችም ይዳከሙና በሂደት በዲፕሎማሲው ቋንቋ ‘Strategic Suffocation’ የሚባለው እንደሚደርስባት ያስቀምጣሉ። 

በቀይ ባህር በአንድ ኮሪደር ብቻ የምትስተናገደው ሀገራችን ከ95 በመቶ በላይ ጅቡቲ ላይ ጥገኛ ስትሆን፤ 25 በመቶ የሚሆነውን የወጪ በጀት ለባህር ክፍያ ታውላለች። 

በሌላ በኩል የባህር በር አለመኖር ሀገሪቱ የራሷ ምስጢር እንዳይኖራት፣ የምታስገባውና የምታስወጣውም በሌሎች ሀገራት ፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአደባባይ ምስጢር እንዲሆን አድርጓል። 

"አናኮንዳውን መስበር" በሚለው የዲፕሎማሲ መርህ ሀገራችን ዓለም አቀፍ ሕግን በተከተለ ከስሜታዊነት በጸዳ አግባብ የትውልዱን ጥያቄ እያስመለሰች ያለችበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል። 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ካለው የተፈጥሮ ሀብት እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። 

በተጨማሪም የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ያለውን ባህር የመጠቀም እና የመሻገር መብት እንዳላቸው በመግለፅ ይህም ባለቤት በሆነው ሀገር እና በቀጣናው ስምምነት ሊደረግ እንደሚችል ያትታል። 

የተጠቀሱትን እና ሌሎችንም ሕጎች መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት እያደረገችው ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክራ እንደምትቀጥል ዶ/ር አብዲ ገልፀዋል። 

በአፎሚያ ክበበው


المواضيع ذات الصلة

ردود الفعل
Top