የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበርነት የሦስቱ እጩዎች አጀንዳ

شهر 1 منذ
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበርነት የሦስቱ እጩዎች አጀንዳ

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ሕብረት ከተቀየረ በኋላ አህጉራዊ ውህደትን ሊያፋጥኑ የሚችሉ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ መዋቅሩንም የአፍሪካን ሰላም እና ዕድገት ሊያሳልጥ በሚችል መልኩ አስተካክሎ እየሠራ እንደሚገኝ ነው ሕብረቱ የሚያወሳው፡፡

የሕብረቱ ኮሚሽን በሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር፣ ኮሚሽነሮች የተዋቀረ ሲሆን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫ በየአራት ዓመቱ የሚካሄድ ነው፡፡

አንድ ሰው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆኖ መቆየት የሚችለው በአጠቃላይ ለስምንት ዓመታትን ብቻ ነው። ይህ ማለት አንድ ሰው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫን መሳተፍ የሚችለው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡

የኮሚሽነር ምርጫው በምስጢር ድምፅ በመስጠት የሚከወን ሲሆን አሸናፊ የሚሆነው ሰው 3/4ኛ ወይም ከ50 አባል ሀገራት መካከል የ36 ገደማ ሀገራትን ድጋፍ ማግኘት ይኖርበታል።

እየተገባደደ ባለው የፈንጆች ዓመት የቀድሞ የቻድ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሙሳ ፋኪ መሃማት የሁለት ዙር ኮሚሽነርነታቸው ስለሚለሚጠናቀቅ ቦታቸውን ለአዲስ ኮሚሽነር ያሰክባሉ።

ሙሳ ፋኪ ማሃመትን ለመተካት ሶስት እጩዎች ቀርበዋል። እነሱም የኬንያው ራይላ ኦዲንጋ፣ የጅቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሀሙድ አሊ የሱፍ እና የቀድሞ የማዳጋስካር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ጀምስ ናቸው፡፡

ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ሦስቱም እጩዎች ነገ በቴሌቪሽን ቀርበው ኮሚሽነር ሆነው ቢመረጡ ሊያሳኳቸው ባሰቧቸው ጉዳዮች ላይ ክርክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እጩዎቹ ኮሚሽነር ሆነው ቢመረጡ ምን ሊያሳኩ አስበዋል?

ራይላ ኦዲንጋ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሆነው ቢመረጡ አህጉራዊ ውህደት፣ መረጋጋት እና ደህንነት እንዲኖር እንደሚሠሩ ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ቁልፉ መሰረታዊ ያለመረጋጋት ምንጮችን መፍታት እና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ነው የሚሉት ኦዲንጋ ይህን ለማሳካት አበክረው እንሚሠሩ ተናግረዋል።

የዘላቂ እና ፍትሀዊ (equitable) ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲኖር እንደሚሠሩ የሚያነሱት እጩ ኮሚሽነሩ አፍሪካውያን የእርስ በእርስ የንግድ ለውውጥን ማሳደግ እና የመሰረተልማት ዕድገትን ማፋጠን እንደሚያስፈልግም ይጠቅሳሉ፡፡

አፍሪካ በፋይናንስ ራሷን ወደመቻል እንድትመጣ የግሉ ዘርፍ ሚና እንዲጎላ እና ሕብረቱ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርግ ፍላጎታቸው መሆኑን በፕሮግራማቸው አሳውቀዋል፡፡

የፆታ እኩልነት እና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመንም ከትኩረት መስኮቻቸው መካከል መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

የጅቡቲ እጩ ማሀሙድ አሊ የሱፍ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሆነው ቢመረጡ ሊያሳኳቸው ያሰቧቸው ጉዳዮችን ጠቅሰዋል፡፡

ተቋማዊ አቅምን ማሳደግ፣ ሰላም እና ደህንነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት፣ የኢኮኖሚ እና የመሰረተ ልማት ዕድገት ላይ በማተኮር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።  

የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲዎችን ማበረታታት፣ አፍሪካን በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚገባትን ቦታ እንድታገኝ ማድረግ፣ የአፍሪካ የትምህርት ፖሊሲን መደገፍ ትኩረታቸው እንደሆነ አስታውቀዋል።

በተለይ ደግሞ የወጣት አህጉር በሆነችው አፍሪካ ከሥራ ፈጠራ ጋር የተያያዙ ፖሊሲዎች ላይ መሥራት አሳካቸዋለሁ ካሏቸው ነጥቦች መካከል ናቸው፡፡

የማዳጋስካሩ እጩ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ደግሞ ሪቻርድ ጀምስ ዋነኛ ትኩረታቸው የአፍሪካ የፖለቲካ እና ደህንነት ጉዳዮች መፍታት እንደሆነ ነው የተናገሩት።

ሕብረቱ ከሌሎች ጥምረቶች እና ትስስሮች እንዲሁም አቻ ተቋማት ጋር በሚኖረው ግንኙነት ሁሉ የአፍሪካን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚሠሩም ገለጸዋል፡፡

የአፍሪካ የሰው ኃይል ዘመኑ የሚጠይቀው እንዲሆን ለማድረግ የሚሠሩ ሥራዎችን ለመደገፍ እና አህጉራዊ ውህደትን የሚያፋጥኑ ተግባራትን እንደሚያከናውኑም ነው ሪቻርድ ጀምስ የገለጹት፡፡

እጩዎቹ በነገው ዕለት በሚደረገው የቴሌቪዥን ክርክር እነዚህን ፕሮግራሞቻቸውን በዝርዝር አቅርበው ይከራከሩበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በለሚ ታደሰ

 


ردود الفعل
Top