የሳንባ ምች (Pneumonia)

أشهر 6 منذ
የሳንባ ምች (Pneumonia)
የሳንባ ምች (ኒሞኒያ) ማለት የሳንባ ኢንፌክሽን ሲሆን፤ ሳንባ በባክቴሪያ፣ በቫይረስ እና በፈንገስ አማካኝነት ሲጠቃ የሚፈጠር ነው፡፡ 
በሽታው እንደ ቀላል ጉንፋን ራሱን ደብቆ ሳንባን የሚጎዳ ሲሆን፤ በራጅ (X-ray) እና ተያያዥ የምርመራ መንገዶች ብቻ ነው ደረጃውን ማወቅ የሚቻለው፡፡
በህብረተሰቡ ዘንድ በተለምዶ "የአየር መጋጨት" ነው ተብሎ ቢታሰብም፤ በዋናነት የሚከሰተው ሳንባ ላይ ኢንፌክሽን ሲከሰት እና በኢንፌክሽኑ ምክንያት ሳንባ ሲያብጥ (ፈሳሽ ነገር ሲቋጥር) የሚከሰት በሽታ ነው፡፡
በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ለመተንፈስ በጣም የሚያስቸግር እና ሲብስም ወደ ሞት የሚያደርስ ነው፡፡
የሳንባ ምች ተላላፊ እና ገዳይ የሆነ በሽታ ሲሆን፤ በተለይ በህጻናት ላይ የሚበረታ ነው፡፡
በአሜሪካ በዓመት 1.3 ሚሊዮን ያክል ሰዎች በሳንባ ምች የሚያዙ ሲሆን፣ ወደ 50 ሺህ የሚጠጉት ደግሞ ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡
በኢትዮጵያ በዓመት ከ3 ሚሊዮን በላይ በሳንባ ምች የሚጠቁ ዜጎች እንዳሉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
በየዓመቱ 40 ሺህ የሚጠጉ ከ5 ዓመት በታች ያሉ ህጻናት በዚሁ በሽታ ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡
 
ምልክቶቹ
👉 ከፍተኛ የሆነ ሳል፤
👉 ትኩሳት እና ላብ፤
👉 የድካም ስሜት፤
👉 የምግብ ፍላጎት መቀነስ፤
👉 ራስ ምታት፤
👉 የአተነፋፈስ ችግር (ለመተንፈስ መቸገር) የመሳሰሉት ናቸው፡፡
 
የሳንባ ምች ዓይነቶች
👉 ከሆስፒታል የሚመጣ የሳንባ ምች፡- አንድ ሰው በሆስፒታል በመቆየቱ ብቻ የሚይዘው የሳንባ ምች ሲሆን፤ ይህ ዓይነቱ የሳንባ ምች ከሌሎቹ ዓይነቶች አደገኛው ነው፡፡
👉 ከማኅበረሰቡ ውስጥ የሚመጣ የሳንባ ምች፡- ይህ ዓይነቱ የሳንባ ምች ጥንቃቄ በጎደለው ጥግግት የሚፈጠር ነው፡፡
👉 የሞቀ ሰውነት ከቅዝቃዜ ጋር ሲጋጭ የሚከሰት የሳንባ ምች፡- ይህ በተለይም በጣም ሞቃታማ በሆነ አካባቢ ማቀዝቀዣ ስንጠቀም የሚከሰት ነው፡፡
👉 በምግብ እና በመጠጥ የሚከሰት የሳንባ ምች፡- ሰዎች የሚመገቡት ምግብ እና መጠጥ ንጽህናውን ያልጠበቀ ከሆነ፤ እንዲሁም የአልኮል ሱሰኛ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚከሰት ነው፡፡
 
የሳንባ ምች ሕክምና
👉 ቀለል ያለ የሳንባ ምች፡- ቀለል ያለ የሳንባ ምች ቤት ሆኖ ወይም የጤና ተቋማት በመሄድ እየተመላለሱ የሚታከመው ሲሆን፤
👉 ከበድ ያለ የሳንባ ምች፡- ከበድ ያለ የሳንባ ምች አብዛኛውን ጊዜ ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ላይ የሚከሰት ሲሆን፤ የአተነፋፈስ ችግር ያለባቸው፣ ራሳቸውን የሳቱ ይሆናሉ፡፡ ሕመማቸው እዚህ ደረጃ የደረሰ ሰዎች ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው በኦክሲጅን በመታገዝ እየተነፈሱ የሚታከሙ ናቸው፡፡
 
ማንኛውም ሰው ከተጠቀሱት የሳንባ ምች መንስኤዎች ራሱን መጠበቅ፣ ከዚህ አልፎ የተጠቀሱትን ምልክቶች ባየ ጊዜ ፈጥኖ ወደ ሕክምና ተቋማት በመሄድ የሕክምና ባለሙያዎችን ማማከር ይኖርበታል፡፡
በሜሮን ንብረት

ردود الفعل
Top