ኢትዮጵያ እና ኬንያ ትብብራቸውን የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለፁ

22 Hrs Ago 139
ኢትዮጵያ እና ኬንያ ትብብራቸውን የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለፁ

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ  በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ጉብኝት በኬንያ አድርጓል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከኬንያ የውጭ ጉዳይና የዲያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትር እንዲሁም የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሙሳሊያ ሙዳቫዲ ጋር ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል ከ60 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ እና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ሁለቱ ሀገራት ትብብራቸውን የበለጠ ለማጠናከር እንዲሁም ለጋራ እድገትና ልማት አዳዲስ መንገዶችን ለመፈተሽ ቁርጠኛ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

በልዑካን ቡድኑ ውስጥ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አንዱአለም ሲያ እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ይገኙበታል።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በጉብኝቱ ወቅት ከኬንያ ኢነርጂ እና ፔትሮሊየም ሚኒስትር ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ በታዳሽ ሃይል እና በዘላቂ ኢነርጂ ልማት ዙሪያ በትብብር ለመስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ምክክር ማድረጋቸውን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።


Feedback
Top