የትምህርት ሴክተር ማነቆዎችን ለመፍታት እየተደረገ ያለው የተቀናጀ ተግባር ውጤት እያስመዘገበ ነው - ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)

2 Days Ago 148
የትምህርት ሴክተር ማነቆዎችን ለመፍታት እየተደረገ ያለው የተቀናጀ ተግባር ውጤት እያስመዘገበ ነው - ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)

''የትምህርት ጥራት እምርታ፤ ለሁለንተናዊ ብልጽግና!'' በሚል መሪ ቃል 1ኛ ዙር ክልላዊ የትምህርት ሴክተር ጉባዔ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ታርጫ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በጉባዔው ላይ፤ የዘርፉን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ በጥራት ማስጠበቂያ ማዕቀፎች ትግበራ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

በክልሉ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻል የተካሄደው ንቅናቄ ውጤታማ ነበር ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የዘርፉ አመራሮችና መምህራን አቅም የማጎልበት ሥራ ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልፀዋል።

በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚስተዋለውን የመማሪያ መጻሕፍት አቅርቦትና ተደራሽነት ለማጎልበት የክልሉ መንግስት የጀመራቸው ሥራዎች በሁሉም የባለድርሻ አካላት ሊታገዝ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው፤ በትምህርት ተደራሽነት እና አግባብነት የተገኘውን አመርቂ ውጤት በጥራት ላይ ለመድገም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በክልሉ በተካሄደው ''የትምህርት ለትውልድ'' ንቅናቄ ከ27 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ ግብአት የማሟላት ሥራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው፤ ጥራቱ የተጠበቀ የትምህርት አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከመቼውም በበለጠ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በሥርዓተ ትምህርት ትግበራ የተስተዋሉ ውስንነቶች፣ የትምህርት አመራሮች ቁርጠኝነት ማነስ እንዲሁም የትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሥራ ምቹ ያለመሆን ሊፈቱ የሚገቡ የሴክተሩ ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

በጉባዔው የሴክተሩ አፈጻጸም ሪፖርት እና የቀጣይ ሥራዎች ዕቅድ ቀርቦ የጋራ ምክክር እንደሚደረግ ተጠቅሷል።

በሰለሞን ባረና


Feedback
Top