በሀረር፣ ጅግጅጋ እና ሌሎች የምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡
ከድሬዳዋ ቁጥር ሁለት - ሀረር- ጅግጅጋ የተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ባልታወቀ ምክንያት ኃይል ማስተላለፍ ማቋረጡን የምስራቅ አንድ ሪጅን የኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች መምሪያ ገልጿል።
የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ወርዲ መሐመድ፤ በተከሰተው ችግር ምክንያት በሀረር፣ ጅግጅጋ እና በሌሎች የምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች ኃይል ተቋርጧል ብለዋል።
ችግሩን ለመለየት ፍተሻ መጀመሩን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን በመጠገን አገልግሎቱን ዳግም ለማስቀጠል ይሰራል ነው ያሉት።
በኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ላይ የተፈጠረው ችግር እስኪፈታ ድረስ ደንበኞች በትግዕስት እንዲጠብቁ ኃላፊው መጠየቃቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመለክታል።