ለሰላም፣ ለውይይትና ለድርድር የምትጠልቅ ጀንበር የለችም፦ አቶ አደም ፋራህ

3 Days Ago 124
ለሰላም፣ ለውይይትና ለድርድር የምትጠልቅ ጀንበር የለችም፦ አቶ አደም ፋራህ
በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ህዝቡ በነቂስ አደባባይ በመውጣት በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ በንፁሀን ላይ ግፍ እየፈፀሙ የሚገኙ ፅንፈኛ ኃይሎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ መንግሥት በተደጋጋሚ እያቀረበው ለሚገኘው የሰላም ጥሪ ድጋፍ እንደሚቸር ድምፁን አሰምቷል።
 
ይህን ተከትሎ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባባሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ህዝቡን "እጅግ በጣም እናመሰግናለን!" ብለዋል።
 
በቀጣይም ክልሉ በተሟላ ሁኔታ ዳግም ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ህብረተሰቡን በማሳተፍ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
 
በመንግሥት በኩል ለሰላም፣ ለውይይትና ለድርድር የምትጠልቅ ጀንበር እንደሌለችም ደጋግመን ማረጋገጥ እንወዳለን ብለዋል አቶ አደም በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልዕክት።
 
ስለሆነም በአማራ ክልል ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት በኃይል አማራጭ የሚገኝ መፍትሔ አለመኖሩን በመረዳት በዛሬው ሰልፍ ጨምሮ ሕዝቡ በተደጋጋሚ እያነሳቸው ያሉ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ፣ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች እየታየ እንደሚገኘው በአስቸኳይ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ ጥሪያችንን እናቀርባለን ብለዋል።

Feedback
Top