ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በክልሎች የሚያደርጉት የመስክ ምልከታ እንደቀጠለ ነው

6 Days Ago 142
ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በክልሎች የሚያደርጉት የመስክ ምልከታ እንደቀጠለ ነው

ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በክልሎች እያደረጉት ያለው የልማት ስራዎች ጉብኝት እና የመስክ ምልከታ እንደቀጠለ ነው።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

በዚህም በወረዳው ካሹ ቀበሌ በክላስተር የለማ የበቆሎ ሰብል፣ የንብ ማነብ ስራ፣ በክላስተር የለማ የቡና ማሳ፣ የሙዝ እርሻ እና የቡና መፈልፈያ ስራዎችን ተመልክተዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በአፋር ክልል ዳሎል ወረዳ የሚገኘው የፖታሽ ማዕድን መገኛ ስፍራን ጎብኝተዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የተመራ ቡድን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በጨንቻ ከተማ በሌማት ትሩፋት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ተዘዋዉሮ ተመልክቷል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የተመራው ቡድን በክልሉ ካፋ ዞን ቦንጋ ከተማና በጊንቦ ወረዳ የተለያዩ የልማት ስራዎችን የጎበኘ ሲሆን፤ የመደመር ትውልድ ቤተመጽሐፍት ግንባታ፣ ቡናን ጨምሮ የተለያዩ ጠቃሜታ ያለቸው ችግኞች ዝግጅት፣ የማር መንደር እንዲሁም የእንስሳት መኖ እና የካፈቾ ብሔር ባህል ማዕከል ግንባታ ምልከታ አድርጓል።

በሲዳማ ክልል የልማት ስራዎችን እየጎበኘ የሚገኘው በቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ የተመራ ቡድን በክልሉ የቱሪዝም ፍሰቱን ለማሳለጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ተመልክቷል።

ቡድኑ በሰሜናዊ ሲዳማ ዞን የመስኖ ልማት እንቅስቃሴዎችንና በሀዋሳ ከተማ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ ያለውን ዘመናዊ ሆቴልና ሪዞርት ጎብኝቷል።

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራት እየጎበኘ የሚገኘው በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የተመራው ቡድን፤ በዞኑ ቃሉ ወረዳ የሌማት ትሩፋት፣ የፍራፍሬ ችግኝ ጣቢያና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ጎብኝቷል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ የለማ የገብስ ማሳን ተመልክተዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚልና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) በአፋር ክልል ዳሎል ወረዳ የሚገኘው የፖታሽ ማዕድን መገኛ ስፍራን ጎብኝተዋል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማኦ እና ኮሞ ልዩ ወረዳ እየተከናወኑ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ስራዎችን የጎበኙ ሲሆን፤ የስንዴ ክላስተር፣ በመስኖ እየለማ ያለ ሽንኩርት፣ የቡና ልማት፣ የንብ እርባታን ጨምሮ የተለያዩ የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ተመልክተዋል።

 


Feedback
Top