የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ጨመረ ወይስ ቀነሰ?

12 Days Ago 194
የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ጨመረ ወይስ ቀነሰ?

በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት እየቀነሰ ቢመጣም በሕብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት እንደሚታይ ይገለፃል፡፡

የህብረተሰብ ጤና ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አምሀ ሀይሌ ከኢቢሲ ዶትስትሪም ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኤች አይ ቪ ኤድስ በ1990ዎቹ ከነበረው የስርጭት መጠንና የሰው ሞት በዓለም አቀፍም ሆነ በሃገር ደረጃ አሁን ላይ 75 በመቶ ቀንሷል ብለዋል፡፡

የኤች አይ ቪ ኤድስ ወረርሽኝ ከፍተኛ በነበረበት ወቅት የነበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ አሁን ላይ ግን የለም በሚባል ደረጃ መቀነሱን ነው የሚናገሩት።

የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት አገልግሎት ላይ ከዋለበት ከፈረንጆች 2005 ጀምሮ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱንም ተናግረዋል። 

በርካታ ሰዎች መድሃኒቱን መጠቀም በመጀመራቸው በሰውነታቸው ውስጥ ያለው የቫይረስ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ሆኗል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በቫይረሱ ከተጠቁት ውስጥ ወደ 91 በመቶ የሚሆኑት እራሳቸውን ያወቁ ናቸው ሲሉም ገልፀዋል።

ከነዚህም ውስጥ 95 በመቶ የሚሆኑት መድሃኒት መጠቀም የጀመሩ ናቸው የሚሉት ዶ/ር አምሀ፤ መድሃኒቱም መጠቀም ከጀመሩት ውስጥ ደግሞ 96 በመቶ የሚሆኑት በሰውነታቸው ውስጥ ያለው የቫይረሱ መጠን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን ወደ ሌላ ሰው የማስተላለፍ እድላቸውም ዝቅተኛ መሆኑን አንስተዋል።

ይህ በመሆኑም የበሽታው ስርጭት በዓለም አቀፍም ሆነ በሃገር ደረጃ የግንዛቤ ፈጠራው  ምንም እንኳን ዝቅተኛ ቢሆንም የበሽታው ስርጭት በፀረ ኤች አይቪ መድሃኒቱ ምክንያት ቀንሷል ሲሉ ተናግረዋል።

በፈንጆቹ 1990ዎቹ መጨረሻ ለይ በኢትዮጵያ በዓመት የሚያዘው የሰው መጠን 100 ሺህ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግን 7 ሺህ 250 አካባቢ መውረድ ችሏል ብለዋል።

በኤች አይ ቪ ኤድስ ዙሪያ ያለው የግንዛቤ ፈጠራ ስራ ተጠናክሮ ቢቀጥልና ወጣቱ  በደንብ ግንዛቤ እንዲኖረው ቢሰራ ግን ከዚህ የበለጠ ለውጥ ማምጣት ይቻል እንደነበረም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ 605 ሺህ 238 ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ በየዓመቱ 7 ሺህ 428 ሰዎች በቫይረሱ እንደሚያዙና ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች በዚሁ በሽታ ምክንያት በየዓመቱ ህይወታቸው እንደሚያልፍ አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው አጠቃላይ የቫይረሱ ስርጭት 0.87 በመቶ ሲሆን በአፍሪካም ዝቅተኛ የሚባል የስርጭት መጠን ያለው መሆኑንም ገልፀዋል።

በሃገሪቱ በተመዘገበው የኤች አይ ቪ ኤድስ የስርጭት ምጣኔ መሰረት አዲስ አበባ በ3.25 በመቶ ከፍተኛ ስርጭት ያለበት ሲሆን ጋምቤላ በ3.24፣ ሀረሪ በ2.76፣ ድሬዳዋ በ2.35 ተከታዩን ደረጃ መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

ቫይረሱ በሰውነታችን ውስጥ ካለ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰውነት ኪሎ መቀነስ እና የበሽታ መከላከል አቅም መዳከም ተጓዳኝ በሽታዎች እና ኢንፌክሽኖች በተደጋጋሚ መከሰት ከምልክቶቹ መካካል ናቸው ሲሉም አመልክተዋል።

አብዛኛውን ጊዜ በኤች አይ ቪ ኤድስ የሚያዙ ሰዎች በሳንባ ነቀርሳ እንደሚጠቁ አንስተው፤ ሁሉም ማህበረሰብ በየጊዜው ምርመራ በማድረግ እራሱን ማወቅ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

በሜሮን ንብረት


Feedback
Top