የአሜሪካ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በቻይና መንግስት ቁጥጥር ሥር እንደሆነ የሚነገረውን የቲክ ቶክ መተግበሪያ በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ላይ እንዲሸጥ ወይም እገዳ እንዲጣልበት የሚያስገድድ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ውሳኔው ለአሜሪካ የፍትህ ዲፓርትመንት ትልቅ ድል እንደሆነ እና ለመተግበሪያው ባለቤት ባይት ዳንስ ኩባንያ ከባድ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ ተጠቅሷል።
የባይት ዳንስ ኩባንያ ንብረት የሆነው እና በአሜሪካ 170 ሚሊዮን የሚደርሱ ተጠቃሚዎች ያሉት ቲክ ቶክ የዜጎችን ግላዊ መረጃዎች ለቻይና መንግስት አሳልፎ ይሰጣል በሚል ለቀረበበት ክስ ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ እንደተደረገበት ነው የተገለፀው፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሜሪክ ጋርላንድ ፍርድ ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ የቻይና መንግስት ቲክ ቶክን በመሳርያነት እንዳይጠቀም ለማድረግ ወሳኝ እርምጃ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
በአሜሪካ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ በበኩሉ፤ ውሳኔው በግልፅ የተካሄደ የንግድ ዘረፋ መሆኑን ገልፆ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን መተማመንና ግንኙነት እንዳይጎዳ አሜሪካ ጉዳዩን በጥንቃቄ መያዝ እንዳለባት አስጠንቅቋል።
በውሳኔው መሰረት ቲክ ቶክ ለአሜሪካ ኩባንያዎች ከመሸጥ ይልቅ መታገድን የሚመርጥ ከሆነ በሚቀጥሉት 6 ሳምንታት ውስጥ በአሜሪካ መስራት ሊያቆም እንደሚችል ተነግሯል፡፡
በአሜሪካ የፍትህ ዲፓርትመንት የተረታው የባይት ዳንስ ኩባንያ ውሳኔውን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ለማለት ማቀቀዱን የዘገበው ሮይተርስ ነው።