ስምምነቱ የተደረሰው በኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የተመራ የልዑካን ቡድን በአዘርባጃን የአላት ነፃ የኢኮኖሚ ዞንን በጎበኘበት ወቅት ነው::
ጉብኝቱ በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ ለገባዉ የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ አሰራሮች፤ ልምድና ተሞክሮዎች የተቀሰሙበት እንደነበር ተጠቅሷል::
የመስክ ምልከታዉ በአላት እና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና መካከል ተቋማዊ ግንኙነት በመፍጠር በቀጣይ በትብብር አብሮ ለመስራት የሚያስችል መደላድል የፈጠረ መሆኑ ተገልጿል::
ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት የተወጣጣዉ ልዑካን ቡድኑ ከአላት ነፃ ኢኮኖሚ ዞን በተጨማሪ ከኢንዱስትሪ ፓርክ ተቋማት ከጥቃቅንና አነስተኛ ኤጀንሲ የስራ ኃላፊዎች ጋር ዉይይትና የመስክ ምልከታ አድርገዋል::
የአላት ነፃ ኢኮኖሚ ዞን በአዘርባጃን ርዕሰ መዲና ባኩ በ719 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና በኢትዮጵያ ከኢንዱስትሪ ፓርክነት ወደ ነፃ የንግድ ቀጣና በማደግ የመጀመሪያ መሆኑ ይታወቃል።