በጎንደር ከተማ አስተዳደር በፌዴራል መንግሥት እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ያለመ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የመሰረተ ልማት አማካሪ አቶ ደሴ አሰሜ እንደገለጹት በፌደራል መንግሰት እየተከናወኑ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ በተነሳሽነት ስሜት ርብርብ ማድረግ ይገባል።
የአዘዞ-አርበኞች አደባባይ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ስራ ተቋራጩ ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ ግብዓቶችን በማሟላት በአጭር ጊዜ መፈፀም እንደሚገባው ገልጸዋል።
በቀጣይ መንገዱን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ሰዓት ተጠቅሞ የተሻለ ለመፈፀም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት የስራ እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ገልፀው፤ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መናገራቸውን የጎንደር ከተማ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።
የጎንደር ከተማ የንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሰራባ ፕሮጀክትን ወደስራ ማስገባት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው፤ የአጭር ጊዜ መፍትሔዎች ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮም በፍጥነት ማከናወን እንደሚገባ ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው፤ በከተማው በፌደራል መንግስት እየተከናወኑ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።