የአድዋ ድል አብሪ ኮከብ፦ ዶጋሊ

منذ 27 أيام
የአድዋ ድል አብሪ ኮከብ፦ ዶጋሊ

የዶጋሊ ጦርነት የተካሄደው የዛሬ 138 ዓመት ጥር 17 ቀን 1879 ዓ.ም ነበር። በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መካከል የተካሄደው ይህ ጦርነት በኢትዮጵያውያኑ አንበሶች ድል ተጠናቀቀ። ጦርነቱ የተካሄደው የዛሬዋ ኤርትራ ውስጥ በምትገኘው በዶጋሊ ከተማ አቅራቢያ ነበር። ይህ ራስ አሉላ አባ ነጋ በሚመሩት ጦር ድል የተጠናቀቀው ጦርነት የአውሮፓ የቅኝ ግዛት ምኞት ኢትዮጵያ ላይ እንደማይሳካ ማየት የተጀመረበት ነበር ይላሉ የታሪክ ተመራማሪዎች።

የኦቶማን ኃይል በአካባቢው ያለው ተጽዕኖ እያሽቆለቆለ በመሄዱ ጣሊያን በቀይ ባሕር ዳርቻዎች ላይ አንዳንድ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር ጥረት ማድረግ ጀመረች። በ1877 ዓ.ም አካባቢም የቅኝ ግዛት ምኞቷ አካል የሆነውን ምፅዋን ተቆጣጠረች። ይህ የጣሊያን እንቅስቃሴም የኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነት በቀጥታ አደጋ ላይ የጣለ ነበር።

አፄ ዮሐንስ አራተኛ የጣልያን መስፋፋት ለኢትዮጵያ ነጻነት ቀጥተኛ ስጋት እንደሆነ ቀድመው ተረድተው እንቅስቀሴ ጀምረው ነበር። ይሁን እንጂ ንጉሡ በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጉዳዮች መጠመዳቸውን ያዩት ጣሊያኖች ከምፅዋ ወደብ ተነስተው ወደ ኤርትራ ደጋማ አካባቢዎች መንቀሳቀስ ጀመሩ።

በኮሎኔል ቶማሶ ደ ክሪስቶፎሪስ የሚመሩት እና 500 የሚሆኑ የጣሊያን ወታደሮች ከወደቡ ተነስተው ወደ ውስጥ መንቀሳቀስ ጀመሩ። ይህን የጣሊያንን እንቅስቃሴ ቀድመው መረጃ ያገኙት ራስ አሉላ አባ ነጋ ጦራቸውን ይዘው በዶጋሊ አቅራቢያ መጠበቅ ጀመሩ። የተደገሰላቸውን ያላወቁት ጣሊያኖችም ብዙም እክል ሳይገጥማቸው እየገሰገሱ ወደ ዶጋሊ አቀኑ። በወቅቱ ከኢትዮጵያ ጋር ሲነፃፀር ዘመናዊ እና በርካታ የጦር መሣሪያ የታጠቁት እንዲሁም ዘመናዊ የውጊያ ሥልት የወሰዱት 500 የጣሊያን ወታደሮች በራስ አሉላ ጦር ቀለበት ውስጥ ገብተው ድባቅ ተመቱ።

ተጠባባቂውን ጦር ጨምሮ ለዘመቻው የተሰለለፉ ወታደሮች እንደወጡ ሲቀሩ፣ የተወሰኑት ብቻ ሊያመልጡ ችለዋል።

ኢትዮጵያ በዶጋሊ የተቀዳጀው ድል የአውሮፓ ቅኝ ግዛት መስፋፋትን መቋቋም የሚችል አስፈሪ ኃይል መሆኗን ያስመሰከረችበት ነበር። ድሉም አፍሪካ በአውሮፓ ቅኝ ግዛት ኃይል ላይ ካገኘቻቸው ታላላቅ ድሎች መካከል አንዱ ነበር። ለኢትዮጵያ ደግሞ የሉዓላዊነቷ ማረጋገጫ እና ለውጭ ኃይል ያለመንበርከኳ ተምሳሌት ሆኗል።

በአንጻሩ ድሉ ጣሊያንን ክፉኛ ያስደነገጠ ሲሆን ለበቀል እና ተጨማሪ ግዛትን ለመያዝ ዝግጅት እንድታደርግ አስገድዷታል። በርካታ የተሻሉ መሣሪያዎች የታጠቁ ኃይሎችን ወደ አካባቢው በመላክ ኃይሏን ማጠናከር ጀመረች። 

ንጉሡ አጼ ዮሐንስ ከመሃዲስት ጋር በነበራቸው እና በሀገር ወስጥ የሚነሳባቸውን አመጽ ለማብረድ እረፍት ባጡበት ሁኔታ ውስጥ ጣሊያን የኤርትራ ይዞታዋን ለማጠናከር በ1882 ኤርትራ ቅኝ ግዛቷ መሆኗን አወጀች።

ይህን ስታደርግ የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ ሚናም ከፍተኛ እንደበር የታሪክ ተመራማሪዎች ያወሳሉ።

በዚህም በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መካከል ያለው ውጥረት ከፍ እያለ መጣ። በተከታታይ በተደረጉ ግጭቶችም በአብዛኛው የኢትዮጵያ ጦር ድል እየቀናው የቅኝ ግዛት ምኞች በዓድዋ ተራሮች ውስጥ ተቀበረ።

የዶጋሊ ድል የጥቁሮች የድል ቀንዲል ለሆነው የዓድዋ ጦርነት መዳረሻ ነበር። ኢትዮጵያ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ መሪነት በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ግምት ከሚሰጣቸው የፀረ ቅኝ ግዛት ድሎች መካከል ወሳኙን ድል ያገኘችበት እና ሌሎችም ለነጻነታቸው እንዲቆሞ ያነቃችበት ነበር።

በዶጋሊ፣ ኮኣቲት፣ ሰናአፌ እና አምባላጄ ላይ በተከታታይ የተመዘገቡት ድሎች በአድዋ ማህተም ተመቶላቸው ተጠናቀቁ። ዶጋሊ ከጊዜ በኋላ ከቅኝ ገዥዎች ጋር ለተደረጉት ጦርነቶች የአንድነትን እና የስትራቴጂያዊ እቅድ ተምሳሌት ሆኗል።

የውጭ ስጋትን ለመከላከል እና በድል ለመወጣት የኢትዮጵያዊያን አንድነት አስፈላጊነት በጦርነቱ ጎላ ብሎ ታይቷል። እንደ ራስ አሉላ አባ ነጋ ያሉ ቆራጥ አመራሮችም በአንደዚህ ዓይነቱ የትግል ሜዳ አስፈላጊ መሆናቸውን አሳይቷል።

ድሉ ኢትዮጵያውያን ከአውሮፓ ኢምፔሪያሊዝም ጋር በሚያደርጉት ትግል ላይ ዓለም አቀፋዊ ትኩረት አግኝተውበታል። ለጣሊያን ሽንፈቱ አሳፋሪ ከመሆኑም በላይ አፍሪካ የቅኝ ግዛት መስፋፋትን ለመፋለም ዝግጁ እንድትሆን ስንቅ ሆኗታል።

ብዙም ሳይቆይ በሌሎች የአህጉሪቱ ክፍሎች ፀረ-ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴዎች እንዲቀጣጠሉም አድርጓል።

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷል ለመከላከል ባደረገችው ትግል ያስመዘገበችው ይህ ድል እንዲገኝ የራስ አሉላ እና የሠራዊታቸው ጀግንነት ወሳኝ ነበር። ይህ ጀግንነታቸውም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በማይፋቅ ቀለም ተጽፎ ለትውልድ እየተላለፈ ዛሬ ላይ ደርሷል:: እነሆ እኛም ከ138 ዓመታት በኋላ እነዛን የአፍሪካን የነጻነት ቀንዲል ያበሩትን ጀግና ልናስብ በመውደድ ጥቂት ታሪካቸውን አስታወስን።

በለሚ ታደሰ


ردود الفعل
Top