ኢትዮጵያ ለትዳር ትልቅ ስፍራ ከሚሰጡ አገራት መካከል አንዷ እንደሆነች በባህል፣ እምነት እና ስነ ልቦና ደረጃ ተግልጦ የሚታይ ነው።
ለዚህም ነው በሃይማኖቶች ውስጥ ትዳር የተከበረ እና ማኅበረሰብ የሚገነባበት የመጀምሪያው ተቋአም እንደሆነ የሚሰበከው።
እናም በትዳር ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮች የሁለት ሰዎች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገር ጉዳይ እና የቀጣይ ትውልድ መነሻ እንደሆነ የሥነ-ልቦና ባለሞያዎች ይናገራሉ።
ለመሆኑ ትዳርን ለማጽናት እና በትውልድ ውስጥ ለመገንባት ምን ማድረግ ይገባል ሲል ኢቢሲ ዶትስትሪም የሃይማኖት መምህራንን አነጋግሯል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሊቃውንት ጉባዔ አባል መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን ሥርዓቷን እና ቀኖናዋን ለማኅበረሰብ የማቅረብ ኃላፊነት አለባት ይላሉ።
ቤተክርስቲያን ከምትሰጠው አገልግሎት ውስጥ ጋብቻ አንዱ እንደሆነ የሚናገሩት መምህር ዳንኤል፣ ትዳር የወንጌል አካል በመሆኑ ምዕመኑን ከማስተማር ጀምሮ ችግሮች ሲኖሩም ቤተክርስትያን እንደምታስታርቅ ተናግረዋል።
“ትዳር ትንሿ ቤተ-ክርስቲያን በመሆኗ ይህን ቅዱስ ነገር ማፍረስ ቤተክርስቲያንን እንደማፍረስ ይቆጠራል” ሲሉ ነው የገለጹት።
ይሁን እንጂ የአስተሳሰብ ለውጦች፣ የባህል መበረዝ እና ሌሎችም ጉዳዮች ተጨምረው ትዳር ሲፈርስ ልናስተውል እንችላለን ብለዋል መምህሩ።
በመሆኑም ባህልን መጠበቅ እና ምዕመኑም እንደየሃይማኖቱ ወደ እምነቱ አስተምህሮዎች ፊቱን መመለስ እና ለሃይማኖት ሕጎች መገዛት እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
የእስልምና ሃይማኖት መምህር የሆኑት ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪ በበኩላቸው፣ ባለትዳሮች አለመቻቻላቸው እና ከፈጣሪ ጋር ያላቸው እምነት መላላት ለፍቺ የሚዳርጉ ምክንያቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገልጻሉ።
"ቀጣዩ ትውልድ ትዳርን የሚፈራ እና ከፈጣሪ ጋር የሚያጋጩ ነገሮች ውስጥ የሚገባ እንዳይሆን እሰጋለሁ" የሚሉት ኡስታዝ የተደከመበት፣ የተለፋበት እንዲሁም ልጆች የተወለዱበት ቤተሰብ እንደቀላል ሲፈርስ ማየት ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።
“ሰው ሆደ ሰፊ መሆን ባለመቻሉ 5 እና 10 ዓመት በትዳር መቆየት ብርቅ ሆኗል” የሚሉት መምህሩ፣ የሃይማት መምህራን በዚህ ጉዳይ ላይ በደንብ ትምህርት ሊሰጡ ይገባቸዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አገልጋይ የሆኑት ነብይ ጥላሁን ፀጋዬ በበኩላቸው፣ “ቤተሰብን የመሠረተው እግዚአብሔር በመሆኑ ይህ ቅዱስ ነገር ሊከበር ይገባል” ብለዋል።
“መጽሐፍ ቅዱስም ሲናገር ‘ፍቺን እጠላለሁ’ ብሏል፤ በመሆኑም የሰው ልጅ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሲያፈነግጥ እና መንፈሳዊ የሆነውን ነገር ሲተው፣ ግለኝነት እና ‘ትክክለኛው እኔነኝ’ የሚሉ ሐሳቦች ሲበዙ ለልጆች እና ለሀገር ማሰብ ሲቆም፣ ለፍቺ መንሥኤ ይሆናል” ብለዋል።
ሙስሊሙ ከመስኪዱ፣ ክርስቲያኑ ከቤተ-ክርስቲያን ፊቱን ሲያዞር ለፍቺ እና ተያያዥ ማኅበራዊ ቀውሶች እንደሚጋለጥ ነው የጠቀሱት።
የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር ጠንካራ ግንኙነት ካለው አጠገቡ ላለ ሰው እና ለቤተሰቡ ያስባል የሚሉት መምህሩ፣ ትውልዱ ሁሉ ወደ ፈጣሪው መመለስ አለበት ሲሉ ገልጸዋል።
በሜሮን ንብረት