ሀረር ከተማን ከፕላስቲክ ቆሻሻ ነፃ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

9 Days Ago
ሀረር ከተማን ከፕላስቲክ ቆሻሻ ነፃ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

ሀረር ከተማን ከፕላስቲክ ቆሻሻ ነፃ ለማድረግና የፕላስቲክ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል የውል ስምምነት በከተማው ማዘጋጃ ቤትና በኪዩቢክ ኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት መካከል ተፈርሟል።

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፤ ስምምነቱ ሀረርን ጽዱ፣ ውብ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በተለይም የፕላስቲክ ቆሻሻ በከተማዋ ጽዳት፣ በእንስሳት፣ በእጽዋትና በአፈር ለምነት ላይ የሚያስከትለውን ከፍተኛ ችግር በመጥቀስ ይህንን በመከላከል ረገድ ስምምነቱ ጠቀሜታው የላቀ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ስምምነቱ ሴቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርግና ፕላስቲክን መልሶ በመጠቀም በዝቅተኛ ዋጋ የመኖሪያ ቤት ለመገንባት እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ ዜጎች ንፅህናው በተጠበቀ ጤናማ አካባቢ እንዲኖሩ አስተዋጽኦ የሚያደርግ በመሆኑ የክልሉ መንግስት ለስምምነቱ ተፈፃሚነት ቁርጠኛ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ቶልቻ በበኩላቸው፤ ደረቅና ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ማዋል እንዲቻል የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በሀረር ከፍተኛ የሆነ የፕላስቲክ ቆሻሻ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ከኪዩቢክ ኩባንያ የተፈጠረው ስምምነት የፕላስቲክ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

ኩባንያው እያከናወነው በሚገኘው ስራም 190 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድልን እንደፈጠረ ገልጸዋል።

ድርጅቱ በከተሞች በጽዳት፣ መኖሪያ ቤትና የስራ እድል ጋር በተያዙ ያሉ ችግሮች ላይ ለውጥ ለማምጣት ይሰራል ያሉት የኪዩቢክ ኩባንያ ዋና ሰራ አስኪያጅ አቶ ቅዱስ ፍሰሃ ናቸው።

በዚህም ሀረርን ከፕላስቲክ ቆሻሻ የጸዳች ለማድረግ በቁርጠኝነት ለመስራት መዘጋጀታቸውን በመግለፅ የክልሉ መንግስት እያደረገላቸው ለሚገኘው ትብብር አመስግነዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top