በቻይና በተከሰተው ከባድ የጎርፍ አደጋ 60 ሺህ የሃገሪቱ ዜጎች መኖሪያቸውን ለቀው እንዲወጡ መደረጉ ተገለፀ

12 Days Ago
በቻይና በተከሰተው ከባድ የጎርፍ አደጋ 60 ሺህ የሃገሪቱ ዜጎች መኖሪያቸውን ለቀው እንዲወጡ መደረጉ ተገለፀ

በቻይና ጓንግዶንግ ግዛት ለቀናት የጣለ ከባድ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ምክንያት የአካባቢው ባለስልጣናት 60 ሺህ የሚጠጉ የሃገሪቱ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ለቀው እንዲወጡ ማድረጋቸው ተገልጿል።

ቅዳሜ እለት በተከሰተው የጎርፍ አደጋ እስካሁን 11 ሰዎች ደብዛቸው የጠፉ ሲሆን በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አልደረሰም ተብሏል።

በመንግስት ሚዲያዎች እና በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ የተቀረጹ ምስሎች በጎርፍ የተጥለቀለቀውን ሰፊ መሬትንና ነፍስ አዳኞች በነፍስ አድን ጀልባዎች ላይ በመሆን የሰዎችን ነፍስ ለማዳን ሲጥሩም ያሳያሉ።

አብዛኛው የጓንግዶንግ ግዛት ፐርል ዴልታ በተባለ ወንዝ የተከበበ ሲሆን፣ ተፋሰሱ በባህር ጠለል መጨመር እና ማዕበል የተነሳ ለጎርፍ ተጋላጭ መሆኑ ተጠቁሟል።

እንደቢቢሲ ዘገባ በጎርፉ አደጋው የግዛቱ ዋና ከተማ ጓንግዙ እንዲሁም ትናንሽ ከተሞች ሻኦጓን እና ሄዩዋን ክፍኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተጠቅሷል።

በግዛቲቱ ቅዳሜና እሁድ ወደ 1.16 ሚሊዮን የሚጠጉ አባወራዎች ኤሌክትሪክ ኃይላቸው ተቋርጦባቸው እንደነበር የተገለጸ ሲሆን እና በግዛቷ ሶስት ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ መደረገም ነው የተገለፀው።

በዋና ከተማዋ ጓንግዙ ውስጥ የሚገኘው ባዩን አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተከታታይ በጣለው ከባድ ዝናብ በረራዎች እንዲሰረዙ እና እንዲዘገዩ መደረጋቸውም የተጠቆመ ሲሆን በጎርፍ አደጋው ግዛቷ 19.8 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንደደረሰባት ተገልጿል።።

የጎርፍ አደጋ የተከሰተባት የጓንግዶንግ ግዛት በቻይና ውስጥ ዋና የማምረቻ ቦታ እና በሀገሪቱ በጣም ብዙ ህዝብ ካላቸው ግዛቶች አንዱ ስትሆን፤ በአጠቃላይ 127 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚኖርባትም ተጠቅሷል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top