ሰሙነ ሕማማት ምንድን ነው? እንዴትስ ይታሰባል?

17 ቀን በፊት
ሰሙነ ሕማማት ምንድን ነው? እንዴትስ ይታሰባል?

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ምዕመናን ከሚጾሙት ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከል ዐቢይ ጾም አንዱ ነው፡፡ "ዐቢይ" የሚለው ቃል ትልቅ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፣ ይህ ጾምም በሁለት ምክንያቶች ትልቅ ጾም እንደሆነ የቤተ-ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ አንደኛው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ጾሞ አርአያ በመሆን ያበረከተው ጾም መሆኑ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ጾሙ ለረጅም ጊዜ ማለትም ሐምሳ አምስት ቀናት የሚጾም ረጅም ጾም መሆኑ ትልቅ ያሰኘዋል፡፡

ጾሙ የሁዳዴ ጾምም ይባላል "ሁዳድ" ሰፊ የመንግሥት እርሻ ወይም ማንኛውም በመንግሥት ትዕዛዝ በብዙ ሕዝብ የሚታረስ እርሻ ነው። ጾሙም ጾመ ሁዳዴ የተባለው ትልቅ እና ረጅም ጊዜ የሚቆይ እንዲሁም ሰውን ለማዳን ሰው በሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ አርአያነት የሚጾም ስለሆነ ነው።

የዐቢይ ጾም 8 ሳምንታት ያሉት ሲሆን፣ በስምንቱም ሳምንታት ያሉ እሁዶች የየራሳቸው ስያሜዎች አሏቸው። የመጀመሪያው እሑድ "ዘወረደ" የሚባል ሲሆን፣ አምላክ ከሰማይ መውረዱን፣ ሰው መሆኑን እና የሰው ልጆችን ለማዳን መከራ መቀበሉን ያወሳል፡፡ ሁለተኛው እሑድ "ቅድስት" ይባላል፤ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ስለሚያወሳ ነው፡፡ የሦስተኛው እሑድ "ምኲራብ" ይባላል፤ በዚህ ሰንበት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምኲራብ ገብቶ "ቤቴ የፀሎት ቤት ይባላል እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት" በማለት በምኩራብ ውስጥ ንግድ ያጧጡፉ የነበሩትን ያባረረበት ነው፡፡ አራተኛው እሑድ "መፃጉዕ" የሚባል ሲሆን 38 ዓመታት ከአልጋ ተጠብቆ የኖረውን መጻጉዕን ፈውሶ "አልጋህን ተሸክመህ ሂድ" ማለቱን የሚያወሳ ነው፡፡

አምስተኛው እሑድ "ደብረ ዘይት" ይባላል፤ ኢየሱስ ክረስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ስለዳግም ምጽዓት ያስተማረው ትምህርት ይታወስበታል፡፡ ስድስተኛው እሑድ "ገብርኄር" የሚባል ሲሆን ‘ገብርኄር’ ማለት የታመነ ባሪያ ማለት ነው፡፡ የጌታውን ብር ተቀብሎ ነግዶ ያተረፈበት፣ በጌታውም ፊት ምስጋናን ያገኘው ሰው ታሪክ ይነገርበታል፡፡ ሰባተኛው እሑድ "ኒቆዲሞስ" ይባላል፣ ኒቆዲሞስ የተባለ የአይሁድ መምህር ቀን ቀን ወገኖቹን ስለሚፈራ በሌሊት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እየመጣ ይማር የነበረውን የሚያስታውስ ነው፡፡ ስምንተኛው እሑድ "ሆሣዕና" ይባላል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጭላ ሆኖ "ሆሣዕና በአርያም" እየተባለ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ለአርባ ቀናት ሆኖ ዐቢይ ጾም እንዴት 55 ቀናት ሆነ?

ከዐቢይ ጾም በፊት ያለው የመጀመሪያ ሳምንት ጾመ ሕርቃል /ኢራቅሊዮስ/ ይባላል። ንጉሥ ሕርቃል በእርሱ የንግሥና ዘመን ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወረርው የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ማርከው ወስደው ስለነበር ይህንን መስቀል ወደ ፋርስ ዘምቶ ለማስመለስ እና ክርስቲያኖች ላይ ይደርስ የነበረውን መከራ ለማቅለል ላደረገው ጦርነት ለመታሰቢያው ይሆነው ዘንድ የተጨመረ ሰባት ቀን አለ። ንጉሥ ሕርቃል ወደ ፋርስ ሄዶ ከመዋጋቱ በፊት ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ነፍስ የገደለ ሰው እስከ እድሜ ልኩ ይጹም ብለው ሥርዓት ሠርተው ነበርና እርሱም ጾሙን ፈርቶ ለመዋጋት ስላልፈለገ በኢየሩሳሌም የነበሩ ምዕመናን በዕድሜው የሚደርስበትን ጾም ተከፋፍለው አምስት አምስት ቀን እንደደረሰባቸው የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡

በዚህም መሰረት ጾመ ሕርቃል እሁድ እና ቅዳሜን ጨምሮ 7 (ጾሙ ከሚገባበት ሰኞ ጀምሮ እስከ እሑድ ድረስ ያሉት ቀናት)፣ ዐብይ ወይም አርባ ጾም (ከቅድስት ሰኞ እስከ ሆሳዕና ዋዜማ ዓርብ ያሉት 40 ቀናት) እንዲሁም የሕማማት 8 ቀናት (ከሆሳዕና ዋዜማ ቅዳሜ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ሥዑር ያለው የኢየሱስ ክርስቶስ መከራ የሚታሰቡባቸው ቀናት) ሲደመሩ 55 ቀን ይሆናል ማለት ነው።

ሕማማት ምንድን ነው? ከመቼ እስከ መቼስ ነው?

ሕማማት የሚባለው ከሆሳዕና ዋዜማ ቅዳሜ እስከ የትንሣኤ ዋዜማ ቅዳሜ ድረስ ያለውን ጊዜ የሚያጠቃልል ነው። ይህ ሳምንት አዳም አትብላ የተባለውን እፀበለስ በልቶ የሞት ፍርድ ከተፈረደበት በኋላ ያሳለፈው 5 ሺህ 500 የፍዳ ዘመን የሚታወስበት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ፍትሃት የለም፣ መስቀል መሳለም የለም፣ በአጠቃላይ ከክርስቶስ ልደት በኋላ የመጡት የድኅነት ምልክቶች በዚህ ሳምንት አይታሰቡም፡፡ ምዕመናንም አፋቸውን እስከሚመራቸው እና የፍዳ ዘመንን ለመሻር ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበላቸውን መከራዎች እስከሚያስታውሱ ድረስ (ፀሐይ እስከምትጠልቅ) ይጾማሉ፡፡

 

ከሰኞ እስከ ትንሳኤ ዋዜማ ያሉት ስድስቱ የሰሙነ ሕማማት ዕለታትም ትርጉም ተሰጥቷቸው ይታሰባሉ፡፡

ዕለተ ሰኞ፡- ይህ ዕለት የቤተ መቅደስ መንጻት እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ ምሳሌውም አንድ በአትክልት ስፍራው የተተከለች በለስ የነበረው ሰው ፍሬ ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም ስላላገኘባት የረገመበት ዕለት ሲሆን፣ የሰው ልጆችም በአምላክ የተሰጣቸውን ሥራ ሠርተው ፍሬ ካላፈሩ ተመሳሳይ ዕጣ እንደሚደርስባቸው የሚያሳይ ነው፡፡

ማክሰኞ፡- ይህ ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረው እና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡

ረቡዕ፡- ይህ ዕለት ደግሞ የአይሁድ ሊቃነ ካህናት እና ጸሐፍት ፈሪሳውያን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ምክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለቱ የምክር ቀን በመባል ይታወቃል፡፡

ሐሙስ፡- ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡ ትሕትና ፍቅር መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳት እና ለማስገንዘብ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡

ዐርብ፡- ዕለቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም እና ለልጆቹ ሲል በቀራንዮ መከራን ተቀብሎ አደባባይ በመስቀል ተሰቅሎ መዋሉን የሚታሰብበት ቀን ነው፡፡ በተለምዶ ስቅለት ወይም ስግደት በመባል ይታወቃል፡፡

ቅዳሜ፡- ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር የዋለባት ዕለት የሚታሰብበት ቀን ስለሆነች “ቅዳሜ ስዑር” ወይም የተሻረች ቅዳሜ ትሰኛለች፡፡ የተሻረች ቅዳሜ የተባለችውም በዓመት አንድ ቀን የሚጾምባት ብቸኛዋ ሰንበት ስለሆነች ነው፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ድንግል ማርያም እና ሐዋርያት እሱን አይሁድ ከያዙበት ሐሙስ ሌሊት ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ድረስ እህል ውኃ አለመቅመሳቸውን ምክንያት በማድረግ ለእሁድ አጥቢያ ሌሊት ስድስት ሰዓት ትንሣኤው ታውጆ ቅዳሴ እስከሚያበቃ ድረስ የምትጾም ብቸኛዋ ሰንበትም ነች፡፡

መልካም የትንሣኤ በዓል!

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top