የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ በአከራይም ሆነ በተከራይ ላይ ጫና በማይፈጥር መልኩ ወደ መሬት እንዲወርድ እንሰራለን፡- ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

16 ቀን በፊት
የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ በአከራይም ሆነ በተከራይ ላይ ጫና በማይፈጥር መልኩ ወደ መሬት እንዲወርድ እንሰራለን፡- ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መጋቢት 24 ቀን የጸደቀው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ መጽደቁን ተከትሎ ለተግባራዊነቱ እየተሰራ መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ገለጸ። 

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ከኢቲቪ 57 ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የዜጎችን መሰረታዊ የመኖሪያ ቤት ችግር ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመፍታት በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። 

ነገር ግን ዜጎች ከገጠር ወደ ከተማ የሚያደርጉት ፍልሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ  እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የመኖሪያ ቤት ፍላጎትም ጨምሯል ብለዋል። 

የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት 80 በመቶውን የግሉ ዘርፍ፣ 20 በመቶውን ደግሞ መንግሥት እንዲያለማ ስትራቴጂ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት። 

የመኖሪያ ቤት ግንባታ ክፍተቱን ለመድፈን በመንግሥትና በግል አጋርነት በቅንጅት እየተከናወነ ያለው ስራም ውጤታማ እየሆነ ነው ብለዋል። 

በየትኛውም ሃብታም አገር ሁሉንም ሰው የመኖሪያ ቤት ባለቤት ማድረግ አይቻልም የሚሉት ሚኒስትሯ፤ ዜጎች በአቅማቸው የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖሩ ለማስቻል የኪራይ ቤቶችን በአማራጭነት ለማቅረብ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል። 

በአደጉ አገራት ሰራተኞች ከደመወዛቸው ከ20 እስካ 30 በመቶ ለቤት ኪራይ ወጪ የሚያደርጉበት ልምድ ተወስዷል ያሉት ወ/ሮ ጫልቱ፤ እንደኛ ባሉ አገራት ደግሞ ሰራተኛው ሙሉ ደመወዙን ለቤት ኪራይ ወጪ ሊያደርግ እንደሚችል አንስተዋል። 

ይህ ችግር በሰራተኛው ህይወት ላይ ማህበራዊ ቀውስ እየፈጠረ በመሆኑ የመንግስት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ሆኗል ነው ያሉት ሚኒስትሯ። 

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጁ በአከራይም ሆነ በተከራይ ላይ ጫና አይፈጥርም ያሉት ሚኒስትሯ፤ ትክክለኛና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ወደ መሬት እንዲወርድ እንሰራለን ብለዋል። 

አዋጁ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በክልሎች ዋና ከተሞች እና በዞን ዋና ከተሞች እየተፈተሻ እንደአስፈላጊነቱ ወደ ሌሎች ከተሞችም እየሰፋ ይሄዳል ብለዋል። 

በመሐመድ ፊጣሞ


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top