ኢትዮጵያዊ ዜግነት

10 Days Ago
ኢትዮጵያዊ ዜግነት

ዜግነትን በሰዎችና በሀገር መሀከል ያለውን ግንኙነት የሚፈጠርበትን የሚያስከትለውን መብትና ግዴታ እንዲሁም የሚያበቃበትን  አግባብ የሚመለከት ሕጋዊ ግንኙነት ነው ብለን ልንተረጉመው እንችላለን።

ስለምንኮራበት ኢትዮጵያዊ ዜግነታችንም በሕገ-መንግስታችን በአንቀጽ 7 እና 33 ላይ የተደነገገ ሲሆን ይህ የዜግነት ግንኙነት የሚፈጠርበት ሁኔታና ውጤቱን በተመለከተ ደግሞ በዜግነት አዋጁ ላይ ዝርዝር ድንጋጌዎች ተቀምጠዋል።

ለመሆኑ  ሕጉ ስለ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ምን ይላል? 

ኢትዮጵያዊ ዜግነት በሁለት መንገድ ሊገኝ ይችላል፡፡ በተወላጅነት እና በሕግ በሚሰጥ ዜግነት።

  1. በተወላጅነት የሚገኝ ዜግነት

በሕገ መንግስታችን በአንቀጽ 7(1) መሠረት ሁለቱም ወላጆች ወይም አንደኛው ወላጅ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ብቻ ልጅ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያገኛል፡፡

በአንዳንድ ሀገሮች ሕግ በሀገራቱ ግዛት ውስጥ በመወለድ ብቻ ዜግነት የሚገኝ ሲሆን የኢትዮጵያ ዜግነት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በመወለድ ብቻ አይገኝም።

በእናትና በአባት በኩል ወይም በአንደኛቸው በኩል የኢትዮጵያዊ ልጅ መሆንን ይጠይቃል፡፡የትም ተወለድ ከኢትዮጵያዊ ከተወለድክ በቃ ኢትዮጵያዊ ነህ ነው ነገሩ፡፡

ዝርዝር የዜግነት ጉዳዮችን ለመወሰን ታህሳስ 13 ቀን 1996 ዓ.ም የወጣው የኢትዮጵያ የዜግነት አዋጅ ቁጥር 368/96 አንቀጽ 3(2) ላይ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ኢትዮጵያ ውስጥ በመወለድ ባይገኝም፤ በሀገራችን ግዛት ተጥሎ የተገኘ ህፃን የውጭ ሀገር ዜጋ መሆኑ ካልተረጋገጠ በስተቀር ወላጆቹ ባይታወቁም ከኢትዮጵያዊ እንደተወለደ ተቆጥሮ የኢትዮጵያ ዜግነት ይኖረዋል ሲል ይደነግጋል፡፡

  1. በሕግ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ዜግነት

ሕገ መንግስታችን የውጭ ሀገር ዜጎች የኢትዮጵያችንን ዜግነት ሊያገኙ እንደሚችሉና ዝርዝሩ በሕግ እንደሚወሰን በአንቀጽ 7(2) እና 33(4) ላይ ደንግጓል፡፡

በሕግ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ዜግነት በዜግነት አዋጁ ከአንቀጽ 5-12 ድረስ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት በማመልከቻ የሚገኝና የኢትዮጵያ መንግስት መስፈርቱን አሟልቷል ብሎ ለሚያምንበት የውጭ ሀገር ዜጋ ቃለ መሀላ አስምሎ የሚሰጠው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡

በሕግ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ለማግኘት ምን ያስፈልጋል?

በዜግነት አዋጁ አንቀጽ 5 መሠረት ዜግነታችሁን ስጡኝ ኢትዮጵያዊ ልሁን የሚል ካለ የሚከተሉትን ማሟላት አለበት፡

ሀ. እድሜው 18 ዓመት የሞላውና በፍ/ቤት ውሳኔ  መብቱን ከመጠቀም ያልተከለከለ፣

ለ. መደበኛ ሥራ ወይም መኖሪያውን በሀገራችን ያደረገና ዜግነት እንዲሰጠው ከማመልከቱ በፊት ባለው አምስት ዓመት ውስጥ ቢያንስ አራቱን በሀገራችን የኖረ፣

ሐ. ከሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋዎች በአንዱ መግባባት የሚችል(መስማትና መናገር)፣

መ. እራሱንና ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበት ሕጋዊ ገቢ ያለው ሰው ( በኔ ግምት የዚህ መስፈርት ምክንያት ደሀ ያጣን ይመስል ያጣ የነጣ ሁሉ ጊዜ ማሳላፊያ እንዳያረገን ይመስላል)፣

ሠ.  መልካም ሥነ-ምግባር ያለውና በወንጀል ያልተቀጣ፣

ረ. የቀድሞ ዜግነቱን የተወ ወይም ዜግነት የሌለው ወይም ዜግነታችንን ቢያገኝ  ዜግነቱን የሚተው መሆኑን የሚያስረዳ መሆን አለበት።

3.ከዜግነት ጋር የተያያዙ የመብት ጥበቃዎች

ዜግነታችን ካለፍቃዳችን ሊገፈፍ ወይም ሊነጠቅ እንደማይችል ሕገ መንግስታችን በአንቀጽ 33(1) ላይ ደንግጓል፡፡

በተጨማሪም ድርብ ዜግነትን መያዝ በኢትዮጵያ አይፈቀድም። ዜግነታችንን የፈለገ አንዱን መምረጥ አለበት፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከሀገራችን ዜጋ ጋር ለሁለት ዓመት የፀና ጋብቻ ያለው ሰውና ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ለማግኘት ከማመልከቱ በፊት ቢያንስ ለአንድ ዓመት በሀገራችን የኖረ የውጭ ሀገር ዜጋ በሕግ ዜግነታችንን ለማግኘት ማመልከት ይችላል።

ኢትዮጵያውያን የሌላ ሀገር ዜጋ በማግባታቸው የሀገራቸውን ዜግነት እንደማያጡም በሕገ መንግስታችን አንቀጽ 33 ላይ ተደንግጓል።

በኛ ዜጋ ጉዲፈቻ የተደረገ ሕፃንም አስራ ስምንት ዓመት ካልሞላው፣ በሀገራችን የሚኖር ከሆነ፣ አንደኛው ጉዲፈቻ አድራጊው የውጭ ሀገር ዜጋ ከሆነ እና በጽሑፍ ከተስማማ ኢትዮጵያዊ መሆን ይችላል።

ለሀገራችን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከተ ሰው፣ በሀገራችን ለአራት ዓመት ባይኖርም አንዱንም ቋንቋችንን መናገር ባይችልም ባበረከተው አስተዋፅዖ መሰረት ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንዲሰጠው ካመለከተ ዜግነታችንን ሊያገኝ ይችላል፡፡

  1. በሕግ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን የማግኘት ሂደት

 በሕግ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ለማግኘት ማመልከቻዉ ለኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት የሚቀርብ ሲሆን ማመልከቻዉ ተቀባይነት ካገኘ ዜግነቱን ለማግኘትና በአዋጁ አንቀጽ 12 መሠረት አመልካቹ መሀላ መፈፀም አለበት፡፡

እንዲህ ብሎ፡-

" እኔ እገሌ እንቶኔ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክሪያሳዊ  ሪፐብሊክ ታማኝ ዜጋ ለመሆንና ለሀገሪቱ ሕገ መንግስት ተገዢ ለመሆን ቃል እገባለሁ፡፡"

መንግስት በሕገ-መንግስቱ 33(2) እና በዜግነት አዋጁ አንቀጽ 14 መሠረት ለዜጎች መብቶችና ሕጋዊ ጥቅሞች ጥበቃ የማድረግ፣ በውጭ ያሉ ዜጎች መብቶችና ሕጋዊ ጥቅሞች የሚረጋገጡበት እርምጃዎች የመውሰድ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡

በተጨማሪም ዜጋችን ለሌላ መንግስት ተላልፎ መሰጠት እንደሌለበትና በኛው ሕግ፤ በኛው ስርዓት መዳኘት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡

በዜግነት አዋጁ አንቀጽ 18 ዜግነታችንን ያገኘንበት መንገድ ከግምት ሳይገባ የኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለን ሁሉ እኩል የዜግነት መብት አለን፡፡

 5.የኢትዮጵያ ዜግነትን መተው

ሕገ-መንግስቱ ካስጠበቃቸው የዜግነት መብቶች አንዱ በአንቀጽ 33(3) መሰረት ኢትዮጵያዊነታችንን መተው ነው። ካልፈለግነው ግድ የሚለን የለም፡፡

ሆኖም ግን አዋጁ ኢትዮጵያዊነትን ብንተው የሌላ ሀገር ዜግነት ያገኘን ወይም ለማግኘት ቃል የተገባልን እንድንሆን በአቀጽ 19 ላይ ደንግጓል፡፡

ዜጎች ዜግነት አልባ እንዳንሆን ለመከላከል ይመስላል፤ ሕግ አስቀድሞ ሌላ ዜግነት እንደምናገኝ ሳያረጋግጥ ዜግነታችንን እንዳንተው የፈለገው።

ይህን መስፈርት ማሟላታችን ከተረጋገጠ በኋላ ደግሞ ዜግነታችንን መተዋችንን የሚገልፅ ቅፅ መሙላት ግድ ነው፡፡

በተጨማሪም:-

-       የሚፈለግበት ብሔራዊ ግዴታ ካለ በቅድሚያ መወጣቱን ማረጋገጥ

-       በወንጀል የተከሰሰ ወይም የተፈረደበት ሰው ከሆነ ደግሞ ነፃ መሆን ወይም ቅጣቱን መፈፀም የግድ ነው፡፡

እነኚህን ቅድመ ሁኔታዎች ካላሟላ የዜግነት መልቀቂያ አይሰጠውም፡፡

የሌላ ሀገር ዜግነት ያገኘ ሰው ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 20(1) መሰረት ድርብ ዜግነት ስለማይፈቀድ አውቆና ፈቅዶ ኢትዮጽያዊ ዜግነቱን እንደተወው ይቆጠራል፡፡

ለአካለ መጠን ያልደረሰና በአንድ በኩል ከውጭ ሀገር ዜጋ የተወለደ ወይም በውጭ ሀገር የተወለደ ልጅ ለአካለ መጠን በበቃ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሌላ ሀገር ዜግነቱን ካልተወ በቀር ፈቅዶ ኢትዮጵያዊነቱን እንደተወው ይቆጠራል።

ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ከሌላ ሀገር ዜግነት ጋር ደርቦ የተገኘ ሰው ደግሞ ኢትዮጵያዊነቱ ቀሪ እስኪደረግ ድረስ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ይቆጠራል፡፡

አንድ ሰው ዜግነቱን ማጣት ወይም መተው የግሉ ውሳኔ ሲሆን የትዳር ጓደኛውና ልጆቹ ዜግነት ላይ የሚያስከትለው ውጤት እንደሌለ በአዋጁ አንቀጽ 21 ላይ ተደንግጓል፡፡

  1. የተውትን ኢትዮጵያዊ ዜግነት መልሶ ማግኘት ይቻላል?

አዎ! በዜግነት አዋጁ አንቀጽ 22 መሰረት ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ትቶ በሕግ የሌላ ሀገር ዜግነት አግኝቶ የነበረ ሰው በመደበኛነት ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሪያውን ከመሰረተ፣ይዞት የነበረውን ዜግነት ከተወና ኢትዮጵያዊነቴን መልሱልኝ ብሎ ካመለከተ ዜግነቱን መልሶ ያገኛል፡፡

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top