በ1998 በድሬዳዋ ከተማ ተከስቶ በነበረው የጎርፍ አደጋ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።
በአደጋው ሰባት የቤተሰብ አባላትን ማጣታቸውን እና አንድ የቤተሰብ አባላቸውን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች ዛፍ ላይ ተንጠልጥለው በሕይወት መትረፍ መቻላቸውን የነገሩን የከተማዋ ነዋሪ አቶ በያን ተሰማ ከማል፣ "በወቅቱ ብዙ ዛፍ ቢኖር ብዙ ነፍስ በጎርፍ አይወሰድም ነበር" ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ።

አቶ በያን ለኢቢሲ እንደገለጹት ዛፍ መትከል የጀመሩትም በጊዜው በተከሰተው አደገኛ ጎርፍ ሕይወታቸውን ያጡ ሰባት የቤተሰብ አባሎቻቸውን እና ሌሎች ወገኖችን በማሰብ ነው።
ያኔ የተከሰተውን ጎርፍ ለማምለጥ ዛፍ ላይ ተንጠልጥለው በሕይወት የተረፉትን በማየትም ‘ዛፍ ሕይወት ነው’ በሚል እሳቤ የችግኝ ተከላ ሥራ ጀመሩ።

አቶ በያን ዛሬ ላይ ከሁለት ሔክታር በላይ ሙሉ በሙሉ ዛፍ በመትከል የዱር እንስሳት እና አዕዋፍ የሚኖሩበት፣ የጎርፍ አደጋንም መከላከል የሚያስችል የ“ኢሊናም ፓርክ” ባላቤት መሆን ችለዋል።
ይህ ፓርክ በጊዜው የቤተሰባቸውን ሕይወት ያተረፈችው ዛፍ ዙሪያን ያካለለ ሲሆን “ያቺ ዛፍ በሕይወት ለተረፉ ወገኖቼ ባለውለታ እና ለ“ኢሊናም ፓርክ” መነሻ ነች ይላሉ አቶ በያን።
ሀብታቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ጊዜያቸውን በሙሉ ዛፍ ለመትከል እና ለመንከባከብ በማድረጋቸውም "በእንጨት ተለክፏል፤ አሳክሙት” መባላቸውን አስታውሰው፣ “ዛሬ ላይ ግን ውጤቱን አይተው አድናቂዎቼ በዝተዋል” ይላሉ።

ሁሉም ሰው ዛፍ እንዲተከል መደረግ አለበት የሚሉት አቶ በያን፣ ችግኝ የሚቆርጥ ወይም ጉዳት የሚያደርስበት አካል ላይ ቅጣት እንዲጣል የሚያስችል ሕግ መወጣት እንዳለበትም ይናገራሉ።
አሁንም እስከ 2018 ዓ.ም ሦስት ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የያዙትን ዕቅዳቸውን እውን እንደሚያደርጉ ገልጸው፣ ለዚህም ችግኝ በብዛት እና በጥራት እያዘጋጁ እንደሆነ ነግረውናል።
በአሁኑ ጊዜ በከተሞች ለተጀመረው የኮሪደር ልማት ውበት የሚሆኑ የተለያዩ ችግኞችን ማዘጋጀታቸውን የገለጹት አቶ በያን፣ በተለይ በድሬዳዋ የፈላው ችግኝ ለድሬዳዋ አየር ተስማሚ እንደሆነ ጠቁመዋል።
አቶ በያን የኢሊናም ፓርክን ለሚጎብኙ እና ችግኝ ለሚፈልጉ ሰዎች በነፃ እየሰጡ እንደሆነም የገለጹልን ሲሆን፣ ተጠቃሚዎችም ይህንን በማረጋገጥ ብርታታቸውን እና ጥንካሬያቸውን አድንቀዋል።
በትዕግስቱ ቡቼ