ትምህርት እምብዛም የሚዘልቀው ዓይነት ተማሪ አልነበረም፤ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ዝቅተኛ ውጤት ያመጣ የነበረው ተማሪ የሚኒስትሪ ፈተና ላይ ግን ከጎበዝ ተማሪዎች ኮርጆ 96 ከመቶ ያስመዘግባል።
በወቅቱ አባቱ የሚማርበት ትምህርት ቤት በጥበቃ ሕይወታቸውን ይገፉ ነበርና ልጃቸው ከፍተኛ ውጤት በማምጣቱ በወቅቱ ያሳዩት ደስታ ሕይወቱን እና የትምህርት መስመሩን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ይቀይረዋል።
እያወራን ያለነው እጅግ አስገራሚ የሕይወት ውጣ ውረዶችን ስላሳለፈው መምህር ዳኛቸው ሻምበል (‘መምህር ዳኒ’) ነው።
ባለታሪካችን በትምህርቱ ጎበዝ ለመሆን ብዙ ጥሯል፤ ጎበዝ ተማሪዎች "የዓሣ ዘይት ጠጥተን ጎበዝን” ሲሉት ሞክሯል።

“ቴክዋንዶ ስለምሠራ ነው ጎበዝ የሆንኩት” ያለውም አልጠፋም፤ ይህኛው ግን ግራ እጁ እንዲሰበር ምክንያት ሆኖታል።
ክረምቱን በድሬዳዋ ከተማ በሚገኝ ቤተ-መጻሕፍት ጠዋት እየሄደ ማንበብ እና ማጥናት ጀመረ፤ ሒሳብ ደግሞ ተወዳጅ ትምህርቱ ሆነ። እንደ ቀልድ ከሒሳብ ስሌቶች ጋር ተላመደ፤ አላሳፈሩትም፤ እንደዋዛ ይታዘዙት ገቡ።
በቀጣዩ ዓመት ዘጠነኛ ክፍል ሲገባ ደካማ ተማሪነቱ ተገረሰሰ፤ በዚህም 3ኛ በመውጣት የላቡን ፍሬ መብላት ጀመረ።
ከዚህ በኋላ ዳኛቸውን የሚያስቆመው አልነበረም። በሁሉም ትምህርቶች ጎበዝ የሆነው ዳኛቸው በ2007 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቅያ ፈተናን 515 በማምጣት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቅሎ የሜካኒካል ምሕንድስና ደረሰው። ነገር ግን 1 ዓመት ከ6 ወር በላይ ለመማር አልታደለም፤ ምክንያቱ ደግሞ እዚህ ጋር በሱስ ተጠምዶ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቶ ስለነበር ነው።
ከዩኒቨርሲቲ የተባረረው ‘መምህር ዳኒ’ ወደ ቻይና የመሔድ ዕድል አገኘ፤ አባቱ ያላቸውን ገንዘብ ሰብስበው ወደዚያው ላኩት፤ በዚያም የፔትሮሊየም ኢንጂነሪንግ ትምህርቱን ተከታተለ፤ ነገር ግን ሱስ ድጋሚ መሰናክል ሆነበት።

ለሁለተኛ ጊዜ ቻይና የመሔድ ዕድል ያገኘው ዳኛቸው፣ የኮምፒውተር ሳይንስ እዚያው መማር ጀመረ። እንዲያውም የሌሎች ሀገር ዜጎችን ማስጠናት ቀጠለ፤ ግን ሱሱ አሁንም ትምህርቱን በአግባቡ እንዳይቀጥል መሰናክል ሆኖበት በፖሊስ ከተያዘ በኋላ ተባረረ።
ዳኛቸው ከቻይና ሲባረር ለአባቱም ሳይናገር ሕይወቱን በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ አደረገ። ከዚያም ሲጋራ፣ ጫት እዲሁም አደንዛዥ ዕፆችን እና መጠጥን መጠቀም ጀመረ። ግን አልቻለም፤ በወቅቱ ቀድሞ ወደሚያውቃት ቢሾፍቱም ተጓዘ፤ እዚያም ሱሱ በረታበት፤ በልቶ ማደርም ቅንጦት ሆነበት።
ጉዞ ከቢሾፍቱ ወደ አዲስ በአበባ
ከቢሾፍቱ ወደ አዲስ በአበባ ሲጓዝ ነበር የአሁኗ ባለቤቱን በመኪና ውስጥ ተዋወቃት። የከሳው፣ የጠቆረው እና ተስፋ የቆረጠው ዳኛቸው በወቅቱ እንደምትረዳው ቃል ገባችለት ከዚይም የጎዳና ሕይወቱ ማብቂያ ሆነ።

ሕይወቱ መልክ እየያዘ የመጣው ዳኛቸው ተማሪዎች የከበዳቸውን የሒሳብ እና የፊዚክስ ትምህርት ማስጠናት ጀመረ። ከሚያስተምራቸው ተማሪዎች አንዱ ትምህርት ቤታቸው የፊዚክስ መምህራቸው ስለለቀቀ ርዕሰ መምህራቸውን ጠይቆ እንዲያሰተምርራቸው መጠየቁን ተከትሎ መምህር ሆኖ ማስተማሩን ተያያዘው።
ሒሳብ እና ፊዚክስን እንደ ቀልድ ማስተማር ተያያዘው፤ ተማሪዎቹ ወደዱት፤ እቁብ የገቡት ‘መምህር ዳኒ’ እና ሚስቱ 9000 ብር እቁብ ሲደርሳቸው ተቀጥሮ ከሚሠራበት ትምህርት ቤት ለቅቆ በቢሾፍቱ ከተማ ስኩል ኦፍ ማይ ሲድ የሚባል የማጠናከሪያ ትምህርት ቤት ከፍቶ በ16 ተማሪዎች ራዕዩን የማሳካት መንገድ ጀመረ።
በሦስት ወር ውስጥ የተማሪዎቹ ቁጥር ወደ 80 ማደጉን ዳኛቸው ይናገራል። ከዚያም ይህ ቁጥር ወደ ሦስት ክፍሎች አሳደገው፤ የማጠናከርያ ትምህርት በሚሰጥበት ሕንጻን ወደ 24 ሰዓት ግልጋሎት የሚሰጥ ቤተ መጻሕፍት አሸጋገረው።
ሚስቱ ምግብ እየሠራች እና በጋራ ተማሪዎችን ኃላፊነት ወስደው እያሳደሩ የአዳር ጥናት ማከናወን ጀመሩ፤ መምህር ዳኛቸው ያስተማራቸው ከሁለት ሺህ በላይ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት በማምጣት ትልቅ ለውጥ ስለማምጣቱም ያስታውሳል።

በኋላ ላይ ቢሾፍቱ ማጠናከርያ እያስተማረ ሳለ “ማስተማር አትችልም” ተብሎ ትምህርት ቤቱ ተዘጋበት። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ተጓዘ።
በኢዲስ አበባ አሁን ላይ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ጀምሮ በኢትዮጵያ በርካታ ተማሪዎችን በበይነ መረብ አመካኝነት ያስተምራል።
ብዙዎች የፊዚክስ ትምህርት ይከብዳቸዋል፤ እንዴት ነው ይህን ቀለል አድርገህ ማስተማር የቻልከው? ብለን የጠየቅነው ዳኛቸው፣ “ፊዚክስ እኮ ሌላ ተአምር ሳይሆን የቀን ተቀን ሕይወታችን ነው፤ እኔ ደግሞ ሳስተምር የምከተለው መርሕ ነገሮችን የአንደኛ ክፍል ትምህርት ያህል ቀላል አድርጌ አስተምራለው ለዛም ነው፤ ቀላል እና መነጋገሪያ የሆንኩት” ይላል።
ዳኛቸው (‘መምህር ዳኒ’) “መምህርነትን በወረቀት የምታረጋግጠው ሳይሆን የፍላጎት ሞያ ነው” ይላል።
“በእርግጥ አሁን ላይ የኔ ሕልም፣ እኔ ያስተማርኳቸው ተማሪዎች ለውጤት በቅተው ማየትን የሚያህል ደስታ የለኝም። ለወደፊት ግን "ማይ ሲድ" ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ ተግባርን የሚያከናውን ትምህርት ተቋም ይሆናል” ሲልም አክሏል።
በሄለን ተስፋዬ