የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የ3D ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር ለማስገባት በዘርፉ እውቅናን ካተረፈው ከኦስትሪያው ግዙፍ የግንባታ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ባውሚት ግሩፕ ከተባለ ኩባንያ ጋር ተስማምቷል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል፤ ከኩባንያው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የ3ዲ የኮንስትራክሽን ፕሪንትን ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በኦስትሪያ ተወያይተዋል፡፡
አቶ ረሻ ተጨማሪ ተሞክሮ ለመቀመር በጀርመን ሙኒክ ከተማ በተሰናዳው የኮንስትራክሽን ማሽንና ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ላይም ተሳትፈዋል፡፡
ኮርሬሽኑ ከዚህ በፊት የአልሙኒየም ፎርም ወርክ የግንባታ ቴክኖሎጂን ከኦቪድ ጋር በመሆን ከደቡብ ኮሪያ በማስመጣት በስፋት ጥቅም ላይ እያዋለ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የፕሪካስት የግንባታ ቴክኖሎጂን ከዋንኮ ኢታሊ ኩባንያ ጋር በመሆን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም ተጠቅሷል፡፡
የአሁኑን ስምምነት ተከትሎ የ3D ኮንስትራክሽን ፕሪንት የግንባታ ቴክኖሎጂ ኮርፖሬሽኑ ለኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ያስተዋወቀው 3ኛው ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ለመሆን ያስችለዋል ተብሏል፡፡
ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ፍላጎትና በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚታየውን የግንባታ ቴክኖሎጂ አቅርቦት ክፍተት ለመሙላት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተነግሯል፡፡
የ3ዲ የኮንስትራክሽን ፕሪንት ከተለመደው የግንባታ ዘዴ ጋር ሲነጻጸር የግንባታ ወጪን ከግማሽ በላይ የሚቀንስና ውስብስብ አርክቴክቸራል የቤት ዲዛይኖችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችል ተጠቅሷል፡፡
ቴክኖሎጂው 98 በመቶ የሚሆነውን ግብዓት ከሀገር ውስጥ የሚጠቀም ሲሆን፤ ግዙፍ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎችንና የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችን በወራት እድሜ ለማጠናቀቅ ያስችላል መጠቆሙን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡