ከሰሙነ ሕማማት ቀናት አንዱ በሆነው ዕለት ማክሰኞ ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ ዕለቱ "የትምህርት ቀን" ይባላል።
በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ የሃይማኖት ትምህርት ሲማር፣ ሲጠይቅ መሰንበቱን የሚያመለክት መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ይናገራሉ።
በዚህ ዕለት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሥልጣኑ ተጠይቋል። ጠያቂዎቹ የካህናት አለቆች እና የሕዝብ አለቆች ሲሆኑ፣ ጥያቄውም፡- "በማን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?" የሚል ነበር።
ይህ ጥያቄ ክርስቶስ ሰኞ ዕለት ሁለት ነገሮችን ማከናወኑን ተከትሎ የተነሣ ጥያቄ ነው። ይኸውም ኢየሱስ ሲያደርጋቸው የነበሩ ተአምራት እና ድንቅ ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀኗቸው እርሱን ከሮማ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የቀየሱት ሥልት መሆኑን ነው የሃይማኖቱ አባቶች የሚገልጹት።
ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ መቅደስ የነበሩትን ነጋዴዎችን አባርሯል፤ መደባቸውን ገለባብጧል። ነጋዴን ማባረር እና መደብን ማስለቀቅ መንግሥታዊ ሥራ ነው። በመሆኑም ክርስቶስ "በራሴ ሥልጣን ነው" ቢላቸው ፀረ-መንግሥት አቋም አለው በማለት ያን ጊዜ እስራኤልን ሲገዛ ከነበረው የሮማ መንግሥት ዘንድ ለማሳጣት እና ለማጣላት ነበር ዕቅዳቸው።
እርሱ ግን ይህንን ሐሳባቸውን ስለሚያውቅ፣ "የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነው? ከሰማይ ነው ወይስ ከምድር?" ሲል ጠይቋቸዋል። ፈሪሳውያን ላቀረቡለት ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠም። ምክንያቱም ጥያቄው ለከሳሾቹ ዓላማ መሳካት አመቺ ሁኔታን ስለሚፈጥር ጥያቄውን በጥያቄ መልሶላቸዋል።
እነርሱም "ከሰማይ ነው" ቢሉት "ለምን አላመናችሁበትም?" እንዳይላቸው፤ "ከሰው ነው" ቢሉት ደግሞ ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ አባት ይፈሩት፣ እንደ መምህር ያከብሩት ነበርና ሕዝቡ እንዳይጣሏቸው ስለፈሩ "ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም" ብለው መለሱለት። እርሱም "እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም" አላቸው።
ይህን ጥያቄ መጠየቃቸውም እርሱ የሚያደርጋቸውን ተግባራት ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት ሳይሆን ልቡናቸው በክፋት እና በጥርጥር ስለተሞላ ስለነበር እንደሆነ የቤተክርስቲያን አባቶች ያስተምራሉ።
ዛሬም ቢሆን ሰዎች መልካም ሥራን በሠሩ ጊዜ ከልዩ ልዩ ወገኖች የሚመጡ ፈተናዎች ለመልካም ሥራው እንቅፋት ሊሆኑ እንደሚችሉ መገንዘብ እንደሚያስፈልግ መምህራን ይናገራሉ።
በጎ ነገርን የሚሠሩ ሰዎችን አሳልፈው ሊሰጡ የሚፈልጉ ሰዎች ፈታኝ ጥያቄ እንደሚያቀርቡም ከወዲሁ መገንዘብ ይገባል በማለት ይመክራሉ።
በክርስቲያኖች ዘንድም ለቅን ሐሳባቸው ከዓለም ዘንድ ተቃራኒ ነገር እንደሚጠብቃቸው እንዲረዱም "ዓለም የሚወደው የገዛ ወገኑን ነው" የሚለውን የክርስቶስን ትምህርት ጠቅሰው ይመክራሉ።
በለሚ ታደሰ