"ሆሳዕና" የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙ"መድኃኒት” ወይም “አቤቱ አሁን አድን" እንደማለት ነው።
በኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት በዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት የሚከበር በዓል ሲሆን፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዓበይት በዓላት አንዱ ነው።
ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱ እና የመጨረሻው ሳምንት ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ ዋዜማ ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዩ፤ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅ እና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያይቱም ግልገል፣ በውርንጫይቱ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” የሚለውን ትንቢት የሚጠቅሱት የቤተክርስቲያኒቱ መምህራን ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከደብረ ዘይት ቤተ ፋጌ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ ይነገራል።
ኢየሱስ ክርሰቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ደብረ ዘይት ቤተ ፋጌ በደረሰ ጊዜ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ጠርቶ “በፊታችሁ ወደአለችው መንደር ሂዱ፤ ያን ጊዜም የታሰረች አህያ ከውርንጫዋ ጋር ታገኛለችሁ፤ ፍቱና አምጡልኝ” አላቸው።
ደቀ መዛሙርቱም የሰው ንብረት ዘርፈን እንዴት እናመጣለን? ብለው መፍራታቸውን የተረዳው ክርስቶስ “ምን ታደርጋላችሁ? የሚላችሁ ቢኖር ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ፤ ያን ጊዜ ይሰዱአችኋል” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዛቸው አደረጉ።
ልብሳቸውንም በአህያው እና በውርንጫይቱ ላይ አድርገው ኢየሱስ ክርስቶስ በእነርሱ ላይ ተቀመጠ።ሕዝቡም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉለት፤ ዘንባባ እና የዛፎችንም ጫፍ እየቆረጡ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ ሆሳዕና በአርያም” እያሉ ይዘምሩ ነበር። ልብሳቸውን ማንጠፋቸውም ለክብሩ መግለጫ እንደሆነ ሊቃውንቱ ያስተምራሉ።
በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባም ከተማዋ በዝማሬ እና በአመስጋኞች ጩኸት ተናወጠች።
የሕዝቡ ጩኸት እና ደስታ ያበሳጫቸው ፈሪሳዊያን እና አይሁድ የሚያመሰግኑትን ዝም እንዲያሰኝ ኢየሱስ ክርስቶስን ቢጠይቁት እሱም፣ “እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ያመሰግኑኛል” ብሎ እንደመለሰላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሷል።
በዚያም መሠረት አዋቂዎችም ሕፃናትም “ሆሳዕና በአርያም” እያሉ ማመስገናቸው “መድኃኒት መባል ለአንተ ይገባሃል” ማለታቸው ነው ይላሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መምህራን።
በበዓለ ሆሳዕና ከሚነሣው አንድምታ ውስጥ አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጫ ላይ መቀመጡ ነው። እንዲያ ማድረጉ የትህትና መገለጫ እንደሆነ ነው የቤተክርስቲያኒቱ አስተምህሮ የሚያሳየው።
አህያዋን ከነውርንጫዋ “ፈትታችሁ አምጡልኝ” ማለቱ የሰውን ልጅ ከኃጢአት እስራት ለመፍታት የመጣ አምላክ መሆኑን እንደሚያመለክትም ይገለጻል።
ደቀ መዛሙርቱም አህዮቹን ፈትተው ማምጣታቸው አንድም “በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ይሁን” ብሎ የሰጣቸውን ሥልጣነ ክህነታቸውን ሲያመላክት በአህያዋ ላይ ልብሳቸውን ማንጠፋቸው “የምትመች የማትቆረቁር የወንጌልን ሕግ ሰጠኸን ሲሉ ነው” ይላሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት።
ከግለሰብ ደጅ የተፈታችን አህያ “ጌታዋ ይፈልጋታል” ብሎ ያስፈታት በፈጣሪነቱ ወይም ስለፈጠራት ገንዘቡ ስለሆነች ነው ይላሉ አባቶች።
አህያን ያልናቀ አምላክ አማኞችም ከኃጢአት እና ክፋት ርቀው በንጹህ ልብ ቢፈልጉት ማደሪያዎቹ ሊያደርጋቸው ፈቃዱ መሆኑን ለማሳየት እንደሆነም ያመሰጥራሉ።
በዋዜማው ዕለት የቅዱስ ያሬድ ድርሰት ከሆነው ጾመ ድጓ “ሆሳዕና በአርያም፣ ሆሳዕና ለወልደ ዳዊት …’’ በማለት ይዘመራል።
የአህያዋ እና የውርጭላዋ ምሳሌም ብንመለከት ትልቋ አህያ የኦሪት ምሳሌ ናት። ትልቋ አህያ ሸክም የለመደች እንደሆነችው ሁሉ ሕገ ኦሪትም የተለመደች ሕግ ናትና በኦሪት ተመሰለች።
ትልቋ አህያ ሸክም እንደለመደች ሁሉ እስራኤልም ሕግ ለመፈጸም በሕግ ለመራመድ የለመዱ እንደሆኑም ያመላክታል።
አንድም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው ሸክም የበዛበትን አዳምን ለማዳን እንደሆነ ለማመላከት እንደሆነም የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች ያስተምራሉ።
ውርንጭላዋ ደግሞ በሕገ ወንጌል እንደምትመሰል ይነገራል፤ ምክንያቱም ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረታት የሠራት አዲሷ ሕግ ናትና።
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ሕዝቡ ዘንባባ ይዞ “በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው” በማለት ስለተቀበሉት ይህን በማሰብ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዘንባባ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ታድላለች።
በቤተ ክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት ከአራቱም ወንጌል ዕለቱን የሚመለከቱ ምንባባት ይነበባሉ። በሰሙነ ሕማማት ጸሎተ ፍትሐት ስለማይፈጸምም ጸሎተ ፍትሐት የሚደረገው በዚሁ ዕለት ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ለምን ዘባባ ተነጠፈለት?
☞ ዘንባባ ደርቆ እንደገና ሕይወት ይዘራልና የደረቀ የምታለመልም አምላክ ነህ ሲሉ ነው፤
☞ ዘንባባ የሰላም ምልክት ነውና የሰላም አምላክ ነህ ሲሉ ነው፤
☞ ዘንባባ የደስታ መግለጫ ነውና አንተ ደስ የምታሰኝ ኀዘናችንም የምታርቅልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው፤
☞ ዘንባባ እሾሃማ ነውና አንተ ሕያው አሸናፊ አምላክ ነህ ሲሉ ነው፤
☞ ዘንባባ እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል፤ ተምሳሌቱም ባሕርይህ የማይመረመር ነው ሲሉ ነው፤ ይላል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ።
በለሚ ታደሰ