የዲሲው የማደያዎች ጌታ - ኢዮብ ማሞ ካቻ (ዶ/ር)

منذ 2 أيام
የዲሲው የማደያዎች ጌታ - ኢዮብ ማሞ ካቻ (ዶ/ር)

በሕይወት አጋጣሚ እ.አ.አ በ1981 በ13 ዓመት ዕድሜያቸው ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካዋ ኖርዝ ዳኮታ ሲሄዱ ዛሬ የደረሱበት ከፍታ ላይ ደርሰው የታላቋ አሜሪካን ዋና ከተማ ተፅዕኖ ፈጣሪ ይሆናሉ ብሎ ያሰበ ማንም አልነበረም።

ታታሪነትን ከአባታቸው የተማሩት ሰው በጥረታቸው ከነዳጅ ማደያ የትርፍ ሰዓት ሥራ ተቀጣሪነት እስከ በርካታ ነዳጅ ማደያዎች ባለቤትነት የደረሱ ታላቅ ሰው ናቸው።

በዋሽንግተን ዲሲ በነዳጅ ማደያ ባለቤትነት በአካባቢው ያሳደሩት ተፅዕኖ እና ስኬታቸው የበርካቶች መነጋገሪያ አድርጓቸዋል።

ይህ ከምንም ተነስቶ ባለፀጋ የሆኑበት መንገድ ከትንሽ ሥራ ተነስተው ራሳቸውን የትልቅ የትራንስፖርት ድርጅት ባለቤት ካደረጉት አባታቸው ጋር ያመሳስላቸዋል።

የገንዘብ ሀብት ብቻ ሳይሆን የማይነጥፍ የአዕምሮ ሀብት እንዳላቸውም ጽፈው ያሳተሙአቸው በርካታ መጽሐፎቻቸው ምሥክሮች ናቸው።

አባታቸው ማሞ ይንበርበሩ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አውቶብሶችን በማቅረብ በመላው ኢትዮጵያ አገልግሎት የሚሰጠውን የመጀመሪያው የትራንስፖርት ድርጅት ባለቤት ነበሩ።

አስኪ እዚህ ጋር፡-

"አውቶቡሱ ማሞ ካቻ
የት ትሄዳለህ ገርበ ጉራቻ
ምን ልታመጣ ማር በስልቻ
ስንት ይከፈላል ስሙኒ ብቻ"፥ ስለተባለላቸው እና ታታሪነታቸውን ለልጃቸው ስላወረሱት አቶ ማሞ ይንበርበሩ ጥቂት እናስታውስ!

ማሞ ይንበርበሩ (ማሞ ካቻ) አባታቸው የጣልያንን ወራሪ ኃይል ለመከላከል ወደ ማይጨው ዘምተው በጦርነቱ የተሠው ሲሆን፣ እናታቸው በህመም ምክንያት ቀደም ብለው ሞተው ስለነበር ገና በ12 ዓመት ዕድሜያቸው ነበር ያለወላጅ የቀሩት። ጣሊያኖች አዲስ አበባን ሲይዙ ጨቅላውን ማሞን ወደ አዲስ አበባ ይዘውት መጡ።

ታዳጊው ማሞ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ወደ አንዱ ሻይ ቤት ተጠግቶ ብርጭቆ እያጠበ እና እየተላላከ በክፍያ መልክ ምግቡን እያገኘ ኑሮውን መግፋት ጀመረ።

ብልህ እና ፈጣን ልጅ የነበረው ማሞ፣ በሻይ ቤቱ ሥራ ብዙም ሳይቆይ፤ አራት ኩሽኔታ የተገጠመለት እና መቀመጫ ያለው ተሽከርካሪ ሠርቶ፤ ህጻናትን አሳፍሮ እየጎተተ ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ ቴሌኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት (ከአሁኑ ቸርችል ጎዳና እስከ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ) ድረስ እያንሸራሸረ ገንዘብ ማግኘት ጀመረ።

ቆይቶም ሳንቲሙን አጠራቅሞ በእጅ የሚጎተት እና ሕፃናትን በቀላሉ የሚያንሸራሽር ተሽከርካሪ ሠርቶ ራሱ እየጎተተ አገልግሎት በመስጠት የተሻለ ገንዘብ ማግኘት ጀመረ።

ይህን የማሞን ጥረት ያስተዋለ አንድ የጣልያን ጦር መኮንን ወደ ምፅዋ ሲሄድ ማሞን ይዞት በመሄድ፣ ሃያ ብስክሌቶችን ገዝቶ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ረዳው። የሃያ ብስክሌቶች ባለቤት የሆነው ማሞ ብስክሌቶቹን እያከራየ ከበፊቱ የተሻለ ገንዘብ ማጠራቀም ጀመረ።

ጣልያኖች ተሸንፈው ኢትዮጵያን ለቅቀው ሲወጡ መኪኖቻቸውን በችኮላ እየሸጡ ነበርና ወጣቱ ማሞም አንዲት ፎርድ ፒክ አፕ በ108 ብር ገዝቶ ከአዲስ አበባ ወሊሶ እና ወልቂጤ ሕዝብ ማመላለስ ጀመረ። ይህንንም ወደ አውቶቡስ አሳድጎ የትራንስፖርት አገልግሎቱን አጠናከረ።

በአገልግሎታቸውም ከዚያ በፊት የሦስት ቀኑን መንገድ እስከ አንድ ቀን ተኩል በማሳጠር የአገልግሎቱ ተጠቃሚው ሕዝብ ለጉዞ ቀዳሚ ምርጫው የአቶ ማሞ ይንበርበሩ አውቶቡስ እንዲሆን አደረጉ። ይህ ፍጥነታቸው ነበር የአባታቸውን ስም እስኪያስረሳ ድረስ "ማሞ ካቻ" ያስባላቸው።

የአባታቸውን ፈለግ የተከተሉት ኢዮብ እና ስኬታቸው

ኢዮብ ማሞ (ዶ/ር) በሰሜን ዳኮታ በሚገኘው የካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታተሉ። እዚያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ወደ ቺጋጎ በማምራት የኮሌጅ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። የኮሌጅ ትምህርታቸውን እየተማሩ በነበረበት ወቅትም ለበኋላ ሕይወታቸው መነሻ የሆናቸውን የነዳጅ መቅዳት ሥራን በትርፍ ሰዓታቸው መሥራት ጀመሩ።

እ.ኤ.አ በ1987 ሰፊ የኢትዮጵያውያ ማኅበረሰብ ወዳለበት ዋሽንግተን ተዛውረው መኖር ጀመሩ። የዚህን የዋሽንግተን ኑሯቸውን ሁኔታ ሲገልጹም፣ "ድንገተኛ እርምጃ ነበር፤ ዋሽንግተንን በደንብ አላውቃትም ነበር፤ ግን እዚህ ከቺካጎ በተሻለ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ስብጥር ያለበት ስለሆነ በጣም ወደድኩት" ይላሉ። "ሁልጊዜ እንደ አባቴ ነጋዴ የመሆን ፍላጎት ነበረኝ" በማለት የሚገልጹት ዶክተር ኢዮብ፣ "የማውቀው ብቸኛው ንግድ ነዳጅ ማደያ ስለነበር አንድ ነዳጅ ማደያ ለመከራየት ወሰንኩ" ይላሉ።

በኮሌጅ ተማሪነታቸው ወቅት በቆጠቡት እና ከአባታቸው ባገኙት ጥቂት ገንዘብ ነዳጅ ማደያ ተከራይተው ሥራውን ጀመሩ። ያኔ ሁለት ወንድሞቻቸው ብቸኞቹ ሠራተኞቻቸው ሲሆኑ፣ ሁሉም በቀን ለ18 ሰዓታት ይሠሩ እንደነበር ይገልጻሉ።

ቀስ በቀስም የነዳጅ ማደያ ቁጥሮችን እያሳደጉ የመጡ ሲሆን ከ2009 ጀምሮ ደግሞ ፈጣን ዕድገትን በማሳየት በርካታ የነዳጅ ማደያዎችን መቆጣጠር ጀመሩ። አቅማቸውን በመጨመርም በዋሽንግተን ዲሲ ብቻ ያላቸውን የነዳጅ ማደያ ቁጥር ከ25 ወደ 240 አሳድገዋል። በአካባቢው ከሚገኙ ጣቢያዎች ግማሽ ያህሉ የእርሳቸው እንደሆነ ይገለጻል።

በጥንካሬያቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ዶክተር ኢዮብ "የአሜሪካን ሕልም በተግባር የሚኖሩ" ባለፀጋ የሚል ስም አትርፈዋል። ከነዳጅ ማደያ የትርፍ ሰዓት ሠራተኛነት የተነሱት ዶክተር ኢዮብ፣ አሁን በስፕሪንግፊልድ የሚገኘው ካፒቶል ነዳጅ ግሩፕ ዋና አስተዳዳሪ እና ቦርድ ሊቀ መንበር ናቸው።

ብዙ ጊዜ ለጋዜጠኞች መግለጫ መስጠት ባይወዱም ለሚዲያ በሚቀርቡበት ወቅትም ትሁት እና ተጫዋች እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። በዲሲ ከ240 በላይ የሼል እና ኤክሶን ማደያዎችን መያዝ የቻሉት የዲሲው የነዳጅ ንግድ ንጉሥ ዶክተር ኢዮብ፣ "ባለፉት ዓመታት ንግዱን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ችለናል፤ ያገኘናቸውን ዕድሎች ሁሉ ተጠቅመንም አዳዲስ አጋጣሚዎች ፈጥረናል" ይላሉ።

ድርጅታቸው ካፒቶል ፔትሮሊየም ቡድን በሜትሮፖሊታን ዋሽንግተን ዲሲ እና በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ግንባር ቀደም የፔትሮሊየም አከፋፋይ ነው።

ዶክተር ኢዮብ ማሞ "ከሼል እና ኤክሶን ከአንዳቸው ነዳጅ ከገዛህ ከኢዮብ ገዛህ ማለት ነው" የሚባልላቸውም እስከመሆን ደርሰዋል።

ከነዳጅ ንግድ ሥራቸው ባሻገር በስፖርት ኢንዱስትሪ ውስጥ ተሰማርተዋል። በዚህም እ.አ.አ በ2024 ዓ.ም የሜጀር ሊል ሶከር ተሳታፊውን ዲሲ ዩናይትድ ተባባሪ ባለቤት ሆነዋል። በክለቡ፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር ጥረት እያደረጉ ነው። ዓለም አቀፍ የስፖርት ትብብርን ለማጎልበት ቁርጠኝነታቸውን በተግባር አረጋግጠዋል።

እ.አ.አ ከ2019 ጀምሮ ደግሞ የንግድ ዘርፋቸውን ወደ ሪል ስቴት እና ሆቴል ኢንዱስትሪ ለማሳደግ እንቅስቃሴ የጀመሩ ሲሆን፣ በዋሽንግተን ዲሲ ረጅሙን ሁለገብ ሕንጻ ለመገንባት ፕሮፖዛል ማቅረባቸውን ዋሽንግተን ፖስት በወቅቱ ዘግቧል።

ዶክተር ኢዮብ የቁስ ሀብታም ብቻ ሳይሆን የአዕምሮም በላፀጋ እንደሆኑ ያሳተሟቸው በርካታ መጽሐፍት ምስክሮች ናቸው። ከነዚህ መጽሐፍት መካከልም የበዛ ሕይወት፣ ምርጫና ውሳኔ፣ ከጥሪ ወደ ተልዕኮ፣ ሁለንተናዊ ብልፅግና፣ አዲስ ሕይወት፣ የጊዜ አጠቃቀም ጥበብ እና ትኩረት የሚሉት የሚጠቀሱ ናቸው። ከእነዚህ መጽሐፍት አብዛኛዎቹ ወደ አፋን ኦሮሞ ተተርጉመው አማዞን ላይ እየተሸጡ ይገኛሉ።

በለሚ ታደሰ


ردود الفعل
Top