ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ለፊቼ-ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

منذ 3 أيام
ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ለፊቼ-ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ለሆነው ፊቼ-ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
 
ርዕሰ መስተዳድሩ ያስተላለፉት መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል፡-
 
ሲዳማ የስነ ከዋክብት ዑደትን በማጥናትና በመመርመር የወቅቶችን እርዝማኔና ንባሬ በማጥናት ሽርፍራፊ ሰከንዶችን ፥ደቂቃዎችንና ሰዓታትን ቀምረው ቀናትን፥ሳምንታትን ፥ወራትንና አመታትን የሚለኩበት የቀደምት እውቀት ጥግ ማሳያ ለሆነው ፊቼ-ጫምባላላ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!
 
የሲዳማ ህዝብ በርካታ ባህሎችና ትውፊቶች ባለቤት ስሆን ከነዚህም ውስጥ አንዱ የዘመን መለወጫ ፊቼ-ጫምባባላ በዓል አንዱ ነው።
ህዝቡ የቀደምት እውቀት ጥግ ማሳያ የሆነው ፊቼ-ጫምባላላ በዓል ለህዝባችን የጥበብ ጥግ፣ ለሀገራችን ኩራት እና ለአለማችን እንቁ ባህላዊ ቅርስ ነው።
 
ፊቼ- ጫምባላላ በሲዳማ ብሔር የአዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ በዓል ሆኖ የሚከበር ሲሆን በብሔሩ ተወላጆች ዘንድ ለብዙ ሺ ዓመታት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ ባህላዊ ትውፊት ነው።
 
ሲዳማ የራሱ የሆነ ጊዜን፥ወቅትንና ዘመንን የሚቀምርበት ባህላዊ እውቀትና ጥበብ ያለው ህዝብ ሲሆን ይህን ባህላዊ እውቀቱንና ጥበቡን ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሸጋገረ ለዚህ ትውልድ አድርሶታል።
 
የሲዳማ አባቶች (አያንቶዎች)ባህላዊ የስነ ፈለክ (Astronomy )ምርምር እውቀትና ጥበባቸው የረቀቀ ሲሆን የሰማይ ከዋክብትን የፀሐይንና የጨረቃን ህብራዊ ውህደትንና ተናጠላዊ አንድምታን በመመርመር የወቅቶችን እርዝማኔና ንባሬ በማጥናት ሽርፍራፊ ሰከንዶችን ፥ደቂቃዎችንና ሰዓታትን ቀምረው ቀናትን፥ሳምንታትን ፥ወራትንና አመትን የሚለኩበት የሲዳማን የቀን አቆጣጠር ካላንደር የፈጠሩ ናቸው።
 
ያኔ ዓለማችን በዘመናዊ የሳይንስ ፥እውቀትና ቴክኖሎጂ ባልረቀቀበት ዘመን፤አብዛኛውን የአለማችን ህዝቦች ንቃተ ኅሊናቸው ባላደገበት ዘመን፤ በጥንታዊ ኋለቀር የአኗኗር ስርዓት ዘመን ቀደምት የሲዳማ አባቶች /አያንቶዎች/የሰማይን ተፈጥሮዋዊ ምንነት፥የምድርን አቀማመጥ፣ የከዋክብትንና የጨረቃ ሥርዓትና ውሁደት መርምረውና አጥንተው ይሄው ለዛሬው ለኛ ትውልድ ይህን የቀንና የጊዜን መለኪያ ባህላዊ ጥበብ አድርሰዋል።
 
ይሄም የሲዳማ ባህላዊ የቀን አቆጣጠር ጥበባዊ እሴት ትንታኔ በአለም አቀፍ ቅርስነት መመዘኛዎች የሚመጥን ሆኖ በመገኘቱ ከዛሬ አስር አመት በአለም አቀፍ ቅርስነት በUNESCO በማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱ ሆኖ ሊመዘገብ አስችሏል፤ በተጨማሪም የአለም የጋራ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ከሚደረግላቸው እና እውቅና ካገኙ አለም አቀፍ ቅርሶች አንዱ ለመሆን በቅቷል።
 
በሲዳማ ብሔረሰብ በፊቼ -ጫምበላላ በዓል ለተፈጥሮ እፅዋትና ስነ ምህዳር ልዩ እንክብካቤና ጥበቃ የሚደረግና የሴቶችና ህፃናት መብት የሚከበርበት ወቅት ሲሆን ለደን ፥ለአፈና ለውሃ ጥበቃ እንዲሁም ለተፈጥሮ የሚሰጠው ክብር የላቀ በመሆኑ እነዚህ ባህላዊ እሴቶች ተተንትነው ፊቼ -ጫንባላላን በአለማቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ ካስቻሉት ነጥቦች የተወሰኑቱ ናቸው።
 
ፊቼ -ጫምባላላ ከአሮጌው አመት ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ የዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን በዓሉ ሲከበር ቂም፥ቁርሾና በቀል ይዞ ወደ አዲሰ ዘመን መሻገር ስለማይፈቀድ የሲዳማ ህዝብ በሁሉቃ ስርዓት ቂም ፥ቁርሾና በቀሉን በይቅርታ የሚያወርድበት በዓል ነው።
 
ስለዚህም የተጣላ የሚታረቅበት፤ ቂም የያዘ ቢኖር ቂሙን የሚረሳበት፤በሰዎች መካከል ይቅርታ ፥መቻቻልና አብሮነት የሚጎለብትበት ፤ፍቅርና መተሳሰብ የሚሰፍንበት በዓል በመሆኑ አሁን በሀገራችን በህዝቦች መሐል እየተከሰተ ላለው ለጥላቻና ግጭት ጉልህ ማስተማሪያ ሊሆን የሚችል ባህላዊ እሴት ነው።
 
በፊቼ -ጫምባላላ የሲዳማ ህዝብ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችን በማቅረብ አቃፊነትፈቱን የሚያንፀባርቅበት ፤ በህብረተሰቡ መሀከል ወንድና ሴት ተብሎ የፆታ ልዪነት የማይደርግበት ፤ህፃን ፥አዋቂና አረጋዊ ተብሎ ሳይከፋፍል ሁሉም በአንድ አይን የሚታይበትና አንዲሁም ለእንስሳት ልዩ እንክብካቤ በመስጠት በዓሉ የሚከበርበት ዕለት ነው።
 
ፊቼ- ጫምባላላ ለሲዳማ ብሔረሰብ ተወላጅ ብቻ ሳይሆን አብሮ በሚኖረውም ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ እንድምታ የሚሰጠው ሲሆን ህዝባዊ ፍቅር የሚገለፅበት ፤የተጣሉ የሚታረቁበት እንዲሁም የሰላምና የልምላሜ መገለጫም ጭምር ሆኖ ይቆጠራል።
 
ፊቼ -ጫምባላላ በብሔረሰቡ ተወላጆች ዘንድ የፍቅር፥የሰላም ፥የአንድነት፥ የአብሮነትና የመተሳሰብ ተምሳሌት በመሆኑ በዓሉ በአለም ቅርስነት መመዝገቡ ፋይዳው የጎላ ነው። እንዲሁም የሲዳማን ሀገር በቀል እውቀትና የብሔሩን ባህላዊ የስነ ከዋክብት ጥናት ጠበብትነትን ለአለም ህዝብ የተዋወቀበት ስለሆነ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪያችን መበልፀግ የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል።
 
መንግሥታችን ለባህላዊ ጥበቦችና እውቀቶች ላቅ ያለ ትኩረት በመስጥ በትውልዱ ውስጥ የጋራ አብሮነትን ሊያጠናክሩና ሊያስተሳስሩ የሚችሉ እሴቶችን የመገንባትና የማፅናት ኃላፊነትን ወስዶ እየሰራ ያለ ሲሆን የወንድማማችነትንና የእህትማማችነትን መርህ መሠረት በማድረግ ህብረብሔራዊት ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚያከናውነው የሰላምን ግንባታ አውድ ፊቼ ጫምባላላ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል።
 
የሲዳማ ብሔረሰብ ከአቃፊነቱ ባሻገር እጅግ ተወዳጅና ተናፋቂ የሆነውን የፊቼ- ጫምባላላ በዓል ሚያከብረው በአንድነትና በጋራ በመብላትና በመጠጣት፤ ያለው ለሌለው በማካፈል፤በመረዳዳትና በመተሳሰብ ሲሆን ይሔን አኩሪ የሆነ ደማቅ ባህለዊ ትውፊታችንን በማጉላት አሁንም እንደ ቀድሞው ያጡትን በመደገፍና በመርዳት፤ የአካባቢያችንንና የቄያችንን ሰላም በመጠበቅ ከክፋትና ካተገባ ተግባር ራሳችንን አቅበን በዓሉን በደስታ እያከበር ወደ አዲሱ ዘመን እንሸጋገር እላለሁ።
 
በድጋሚ እንኳን ለሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል በሰላም አደረሰን!
 
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ

ردود الفعل
Top