አፍሪካ ራሷን የመመገብ አቅም እንዳላት ኢትዮጵያ እያስመሰከረች ነው - የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት

منذ 2 أيام
አፍሪካ ራሷን የመመገብ አቅም እንዳላት ኢትዮጵያ እያስመሰከረች ነው -  የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት

አፍሪካ ራሷን የመመገብ አቅም እንዳላት ኢትዮጵያ እያስመሰከረች መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ገለፀ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ ሃገሪቱ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ በዘላቂነት ራስን ለመቻል እየሰራች መሆኗን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት 6 ዓመታት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ግልፅ ፖሊሲዎችን በመተግበር የምግብ ዋስትናን ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት እራስን መቻልን ለማረጋገጥ ያለመ እንቅስቀሴ እያደረገ መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል።

የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድግ ፖሊሲ በመተግበር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ በዘላቂነት ራስን ለመቻል እየተሰራ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ብዙ ጊዜ አፍሪካን በዕርዳታ ላይ ጥገኛ አድርጎ በሚገልጽ ዓለም ውስጥ ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ለመቻል ቆራጥ እርምጃዎችን በመውሰድ ይህንን ትርክት ለመቀልበስ እየሰራች ነው ሲልም መግለጫው አትቷል፡፡

እነዚህ ጥረቶች ኢትዮጵያ ከጥገኝነት ለመላቀቅ እና ዘላቂ ልማትን ለማጎልበት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቁ ናቸው ብሏል መግለጫው።

በዚህ ሂደት አገራዊውን የእድገት ግስጋሴ ለማዳከምና የልማት ጥረቱን በተለይም በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን ተቀባይነትን ለማሳጣት የውጭ ጥረቶች እንደሚደረጉ መግለጫው አስታውሷል።

ይሁንና ሃገሪቱ የጀመረችው በምግብ ራሷን የመቻል ትልም በቁርጠኝነት እንደሚከናወን እና መንግስትም በዚህ ረገድ የማይናወጥ አቋም ይዞ እንደሚንቀሳቀስ መግለጫው  አስገንዝቧል፡፡

ኢትዮጵያ በምግብ እራሷን ለመቻል በምታደርገው ጉዞ የስንዴ ምርታማነት ማረጋገጥ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ያወሳው መግለጫው፤ በዚህም ሀገሪቱ በተገበረችው ውጤታማ እርምጃ የስንዴ ምርታማናቷን እንዳሻሻለችና ለውጭ ገበያ የምታቀርበውም ምርት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉ ተመላክቷል።

በዚህ ረገድ ሃገሪቱ የመስኖ እርሻን በመስፋፋት፣ የተሻሻሉ የዘር ዓይነቶችን በመጠቀም እና ዘመናዊ የአስተራረስ ቴክኒኮችን በመተግበር የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሏ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

አፍሪካ ራሷን የመመገብ አቅም እንዳላት ኢትዮጵያ እያስመሰከረች ነው ያለው መግለጫው፤ የኢትዮጵያ በምግብ እራስን መቻል ሀገራዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገት ወሳኝ እርምጃ መሆኑንም አስገንዝቧል፡፡


ردود الفعل
Top