ለኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት የሚያገለግል የዲጂታል ሰርተፊኬት ይፋዊ ቁልፍ የማመንጨት ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ

منذ 2 أيام
ለኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት የሚያገለግል የዲጂታል ሰርተፊኬት ይፋዊ ቁልፍ የማመንጨት ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ
በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ለሚጀምረው የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት የሚያገለግል የዲጂታል ሰርተፊኬት ይፋዊ ቁልፍ የማመንጨት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
 
የዲጂታል ሰርተፊኬት ይፋዊ ቁልፍ የማመንጨት ሥነ ሥርዓቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገግሎት በቅንጅት አከናውነውታል።
 
ለኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አገልግሎት የሚሆነው የዲጂታል ሰርተፊኬት ይፋዊ ቁልፍ የማመንጨት ሥነ ሥርአት የዓለም አቀፉን የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ስታንዳርድ መሰረት በማድረግ የተከናወነ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ለኢቢሲ በላካው መግለጫ አስታውቋል።
 
በሥነ ሥርዕቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ፤ የዲጂታል ሰርተፊኬት ዋና ጠቀሜታ በይነ-መረብን በመጠቀም የሚካሄደው የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አገልግሎት ለከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ተጋላጭ በመሆኑና በዓለማቀፍ ደረጃ ሕጋዊ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያስችል ነው ብለዋል።
 
ይህ የተካሄደው የዲጂታል ሰርተፊኬት ይፋዊ ቁልፍ የማመንጨት ሥነ ሥርዓት በኢትዮጵያ በቅርቡ የሚጀምረውን የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አገልግሎት አጠቃላይ ደህንነት እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል።
 
በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕጋዊ ተቀባይነትና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችሉ አራት የኢንፎርሜሽን ደህንነት አገልግሎቶችን፤ ማለትም፡ ሚስጥራዊነትን የመረጃን ሙሉዕነትና ትክክለኛነትን ፣የመረጃ ልውውጥ ተሳታፊዎችን ማነንነት ማረጋገጥ እና የመረጃ ልውውጥ መካካድን ማስቀረት የሚያስችል እንደሆነም ገልጸዋል።
 
የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት አገልግሎት በየትኛውም ዓለም ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው በመሆኑ በጉዞ ወቅትና በድንበር ላይ የሚኖሩ አሰራሮችን በእጅጉ እንደሚያቀላጥፈው ተናግረዋል።
 
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ብሔራዊ የሩት ሰርተፊኬት ባለስልጣን ሆኖ በማገልግለ ላይ ሲሆን፤ ለዚህ አገልግሎት የሚሆነውን “የይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማት” የዳታ ማዕከል ነሃሴ 2016 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረጉ ይታወሳል።

ردود الفعل
Top