ኢትዮጵያ 13 ሀገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር እየሰራች ነው - ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀስላሴ

1 Day Ago 128
ኢትዮጵያ 13 ሀገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር እየሰራች ነው - ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀስላሴ

ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዝም ፍኖተ ካርታ 13 ሀገራትን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር እየሰራች መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀስላሴ ገለፁ።

ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀስላሴ በታንዛኒያ በተደረገው የአፍሪካ ታዳሽ ኃይል ጉባዔ የፓናል ውይይት ላይ ተሳትፈዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ወቅት፤ በኢትዮጵያ እምቅ የታዳሽ ኃይል ሀብት መኖሩን ጠቅሰው፤ ሃገሪቱ በኢነርጂ ፖሊሲዋ በተቀናጀ መልኩ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ የታዳሽ ኃይልን ለጅቡቲ፣ ለኬኒያና ለሱዳን እየሸጠች መሆኑንና በቅርቡም ለታንዛኒያ ማቅረብ እንደምትጀምር ተናግረዋል።

በቀጣይ ለሌሎች ሀገራት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

በኢትዮጵያ የታዳሽ ሀይል ፕሮጀክት ህብረተሰቡ ተሳታፊ መሆኑን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፤ የህዳሴ ግድብን ለአብነት አንስተዋል።

ከ5 ቢሊዮን ውስጥም 1 ቢሊዮን ከህዝቡ ተሳትፎ የተገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽ ለማድረግ አሁንም ፈታኝ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ 60 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ ከኤሌክትሪክ ኃይል ውጪ ነው ብለዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግስት ብሔራዊ ፕሮግራም በማዘጋጀት ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በየዓመቱ ለ3.4 ሚሊዮን ቤተሰብ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ የከፍተኛ ሀይል ማስተላለፊያ እና ማከፋፊያ ለሀገሪቱ ፈታኝ መሆኑን አንስተዋል።

ተቋማዊ ሪፎርም ማድረግ፣ የግል ዘርፉን ማሳተፍና ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር የመስራት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን ውጤታማ እያደረጋት መሆኑን ለተሳታፊው ገልፀዋል።

በሙሉ ግርማይ


Feedback
Top