ተመድን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት በአንካራ የተደረሰውን ስምምነት አደነቁ

13 Days Ago 213
ተመድን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት በአንካራ የተደረሰውን ስምምነት አደነቁ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ)ን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል በአንካራ የተደረሰው ስምምነት በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት የሚያስችል ነው ሲሉ አድንቀዋል።
 
በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት ድጋፋቸውን እንደሚያደርጉም ነው ያስታወቁት።
 
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አደራዳሪነት የደረሱበትን ስምምነት አድንቆ፣በወዳጅነት እና በመከባባር መንፈስ የተደረገው ውይይት መልካም ጅማሮ መሆኑን ጠቅሷል።
 
በቀጣይ የሚካሄደው የቴክኒካል ውይይት የተሻለ ውጤት ይዞ እንደሚመጣ እምነቴ ነው ያሉት የተቋሙ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች፤ተመድ የውይይት ሂደቱን በየትኛውም መንገድ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።
 
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ስምምነቱን ያደነቀች ሲሆን፣ የሀገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስምምነቱ በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና ገንቢ ትብብር ለመፍጠር አስተዋጽኦ ያደርጋል ብሏል። ሚኒስቴሩ ቱርክ ለተወጣችው የአደራዳሪነት ሚናም አድናቆቷን ቸሯል።
 
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከኢትዮጵያና ሶማሊያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር እንደምትሻ ገልጻ፣ በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት እንደምትሰራም ጠቁማለች።
 
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የአንካራ ስምምነት ለአፍሪካ ቀንድ ሕዝብ መረጋጋትን ለማምጣት የሚያስችል ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን ገልጿል።
 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በቀጣይም ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውይይታቸውን በመተማመን የአጋርነት መንፈስ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል።
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 

Feedback
Top